ዘኁልቍ 28

የየዕለቱ መሥዋዕት

1 እግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ይህን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን ስጣቸው፤ ‘ሽታው ደስ እንዲያሰኘኝ በእሳት የሚቀርብልኝን የምግብ ቊርባን የተወሰነውን ጊዜ ጠብቃችሁ አቅርቡልኝ’ በላቸው።

3 ደግሞም እንዲህ በላቸው፤ ‘በእሳትለእግዚአብሔር(ያህዌ)የምታቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፤ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በየዕለቱ አቅርቡ።

4 አንዱን ጠቦት ጠዋት ሌላውን ደግሞ ማታ አቅርቡ፤

5 ከዚህም ጋር ተወቅጦ በተጠለለ በሂንአንድ አራተኛ የወይራ ዘይት የተለወሰ የኢፍአንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቊርባን አዘጋጁ።

6 ይህም ሽታው ደስ እንዲያሰኝ በእሳትለእግዚአብሔር(ያህዌ)የሚቀርብ ምሥዋዕት ሲሆን፣ በሲና ተራራ የተደነገገ መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

7 ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር አብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቊርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቊርባን በተቀደሰው ቦታ ላይለእግዚአብሔር(ያህዌ)አፍስሱት።

8 ሁለተኛውንም ጠቦት ጠዋት ባቀረባችሁት ዐይነት አድርጋችሁ ከእህል ቊርባኑና ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር ማታ አቅርቡት፤ ይህም ሽታውእግዚአብሔርን(ያህዌ)ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

የሰንበት መሥዋዕት

9 “ ‘በሰንበት ዕለት፣ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የማይገኝባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መሥዋዕት ከመጠጥ ቊርባኑና በዘይት ከተለወሰ የኢፍሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ጋር አቅርቡ።

10 ይህም ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

የየወሩ መሥዋዕት

11 “ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁለእግዚአብሔር(ያህዌ)አቅርቡ።

12 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤

13 እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳትለእግዚአብሔር(ያህዌ)የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢንግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢንአንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

15 ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖለእግዚአብሔር(ያህዌ)ይቀርባል።

ፋሲካ

16 “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀንየእግዚአብሔር(ያህዌ)ፋሲካ በዓል ይከበራል።

17 በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ።

18 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት።

19 እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግለእግዚአብሔር(ያህዌ)አቅርቡ።

20 ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤

21 ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።

22 በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆናችሁ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።

23 እነዚህንም ጧት ጧት በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር አቅርቧቸው።

24 በዚህም ዐይነት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሆኖ በየዕለቱ ለሰባት ቀን በእሳት ለሚቀርብ መሥዋዕት የምግብ ቊርባን አዘጋጁ፤ ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ሆኖ በተጨማሪ ይቀርባል።

25 በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት።

የሳምንቱ በዓል

26 “ ‘በየሳምንቱ በሚደረገው በዓል፣ አዲስ የእህል ቊርባንለእግዚአብሔር(ያህዌ)በምታቀርቡበት በፍሬ በኵራት ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት።

27 ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታውእግዚአብሔርን(ያህዌ)ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ።

28 ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፉ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤

29 ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፉ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቅረብ።

30 በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

31 ከእህል ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ እነዚህን ከመጠጥ ቊርባናቸው ጋር አቅርቡ። እንስሳቱም እንከን የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጡ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *