ዘኁልቍ 36

የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ርስት

1 ከዮሴፍ ዝርያ ጐሣዎች የሆኑ የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ጐሣ የቤተ ሰብ አለቆች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች አለቆች ወደሆኑት መሪዎች ቀርበው ተናገሩ፤

2 እንዲህም አሉ፤ “ምድሪቱን በዕጣ ከፋፍለህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ እንድትሰጣቸውእግዚአብሔር(ያህዌ)አንተን ጌታዬን ባዘዘ ጊዜ የወንድማችንን የሰለጰዓድን ድርሻ ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አዞሃል።

3 ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባል ቢያገቡ ድርሻቸው ከእኛ የዘር ርስት ላይ ተወስዶ የሚያገቧቸው ሰዎች ላሉበት ነገድ ይተላለፋል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በዕጣ ከተደለደለልን ርስት ላይ ከፊሉ ሊቀነስብን ነው።

4 የእስራኤላውያን ዓመተ ኢዮቤልዩ በሚመጣበት ጊዜ የእነርሱ ድርሻ ወደ ባሎቻቸው ነገድ ይጨመራል፤ ይህ ከሆነም ድርሻቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ላይ ይወሰዳል።”

5 ከዚህ በኋላ ሙሴእግዚአብሔር(ያህዌ)በተናገረው መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “የዮሴፍ ነገድ የተናገረው ትክክል ነው፤

6 እንግዲህ የሰለጰዓድን ሴት ልጆች በተመለከተእግዚአብሔር(ያህዌ)የሚያዘው ይህ ነው፤ ከአባታቸው ነገድ ወገን እስከ ሆነ ድረስ የወደዱትን ማግባት ይችላሉ።

7 እያንዳንዱ እስራኤላዊም ከቀደሙት አባቶቹ በወረሰው ርስት ይጽና፤ በእስራኤል ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ የሚተላለፍ ርስት አይኖርም።

8 እያንዳንዱ እስራኤላዊ የየአባቶቹን ርስት መውረስ ስላለበት፣ በማንኛውም የእስራኤል ነገድ ውስጥ ርስት የምትወርስ የትኛዪቱም ሴት፣ ከአባቷ ነገድ ወገን የሆነውን አንዱን ማግባት አለባት።

9 እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የወረሰውን መሬት እንዳለ ማቈየት ስላለበት፣ ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ አይተላለፍም።”

10 ስለዚህም የሰለጰዓድ ሴት ልጆችእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

11 የሰለጰዓድ ሴት ልጆች፤ ማህለህ፣ ቲርጻ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ።

12 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ዝርያ ጐሣዎች ጋር በመጋባታቸው፣ ርስታቸው በዚያው በአባታቸው ጐሣና ነገድ እጅ እንዳለ ቀረ።

13 ከኢያሪኮማዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ በሞዓብ ሜዳ ሳሉእግዚአብሔር(ያህዌ)በሙሴ አማካይነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዞችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *