ዘዳግም 12

ብቸኛው የማምለኪያ ስፍራ

1 የአባቶቻችሁ አምላክእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው።

2 ከምድራቸው የምታስለቅ ቋቸው አሕዛብ በረጅሙ ተራሮች፣ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።

3 መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።

4 በእነርሱ መንገድ አምላካችሁንእግዚአብሔርን(ኤሎሂም ያህዌ)አታምልኩ።

5 ዳሩ ግን አምላካችሁእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ።

6 ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ።

7 በዚያም በአምላካችሁበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁእግዚአብሔር(ያህዌ ኤሎሂም)እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።

8 ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤

9 ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም።

10 ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል።

11 ከዚያም አምላካችሁእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁምለእግዚአብሔር(ያህዌ)የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ።

12 እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ።

13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ።

14 ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣እግዚአብሔር(ያህዌ)በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝህን ሁሉ ጠብቅ፤

15 ሆኖም አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል።

16 ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

17 የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም።

18 አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፤ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፊት ደስ ይልሃል።

19 በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።

20 አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ።

21 ስሙን ለማኖር አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ።

22 ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ።

23 ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ።

24 ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

25 በእግዚአብሔር(ያህዌ)ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው።

26 ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህእግዚአብሔር(ያህዌ)ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ።

27 የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ።

28 በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።

29 የምትወሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣

30 ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳ ትጠመድ ተጠንቀቅ።

31 አምላክህንእግዚአብሔርን(ኤሎሂም ያህዌ)በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩእግዚአብሔር(ያህዌ)የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።

32 እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምር በት፤ አትቀንስለትም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *