1 የሰማያትና የምድር፣ በውስጣቸውም ያሉት ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ።
2 እግዚአብሔር(ኤሎሂም)ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።
3 እግዚአብሔር(ኤሎሂም)ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና።
አዳምና ሔዋን
4 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት እንደዚህ ነበረ፤
እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር
5 የሜዳ ቡቃያ ገና በምድርላይ አልታየም፤ የሜዳ ተክልም ገና አልበቀለም፤ ምክንያቱምእግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)በመሬት ላይ ገና ዝናብ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚያለማ ሰው አልነበረም።
6 ነገር ግን ውሃከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር።
7 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውንአበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።
8 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው።
9 እግዚአብሔርአምላክም(ያህዌ ኤሎሂም)ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ።
10 የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር።
11 የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በሐዊላ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የፊሶን ወንዝ ነው።
12 ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው።
13 ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የግዮን ወንዝ ነው።
14 ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተ ምሥራቅ የሚፈሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።
15 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው።
16 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ።
17 ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።”
18 ከዚህ በኋላእግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)፣ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ።
19 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ።
20 ስለዚህ አዳምለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው።
ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር።
21 እግዚአብሔርአምላክም(ያህዌ ኤሎሂም)በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንትወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው።
22 እግዚአብሔርአምላክ(ያህዌ ኤሎሂም)ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንትሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።
23 አዳምም እንዲህ አለ፤
“እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣
ሥጋም ከሥጋዬ ናት።
ከወንድ ተገኝታለችና ሴትትባል።”
24 ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25 አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።