1 ሳሙኤል 1

የሳሙኤል መወለድ

1 በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ የኤያሬምኤል ልጅ፣ የኢሊዩ ልጅ፣ የቶሑ ልጅ፣ የናሲብ ልጅ፣ ነበረ።

2 እርሱም አንዲቱ ሐና፣ ሌላዪቱ ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍናና ልጆች ሲኖሯት፣ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።

3 ያም ሰው ሁሉን ቻይ ለሆነውለእግዚአብሔርለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስየእግዚአብሔርካህናት ነበሩ።

4 ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር።

5 ሐናን ግን ይወዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂእግዚአብሔርማሕፀኗን ዘግቶት ነበር።

6 እግዚአብሔርማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር።

7 ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደእግዚአብሔርቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር።

8 ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።

9 አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስመቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።

10 ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደእግዚአብሔርጸለየች።

11 እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉለእግዚአብሔርእሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።”

12 ሐና ባለማቋረጥ ወደእግዚአብሔርበጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።

13 እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምጿ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት።

14 እርሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት።

15 ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም።

16 ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭን ቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለ ሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቊጠረኝ።”

17 ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት።

18 እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።

19 በማግስቱ ጠዋት ተነሥተውበእግዚአብሔርፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤እግዚአብሔርምአሰባት፤

20 ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤልአለችው።

ሐና ሳሙኤልን ለእግዚአብሔር ሰጠች

21 ሰውየውም ሕልቃናለእግዚአብሔርዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ።

22 ሐና ግን አልሄደችም፤ እርሷም ባሏን፣ “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄበእግዚአብሔርፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” አለችው።

23 ባሏ ሕልቃናም፣ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥዪው ድረስ እዚሁ ቆዪ፤ ብቻእግዚአብሔርቃሉንያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሐና ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች።

24 ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያዱቄትና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፣ በሴሎ ወዳለው ወደእግዚአብሔርቤት አመጣችው፣ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ።

25 ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት።

26 ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደእግዚአብሔርስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ።

27 ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤እግዚአብሔርምየለመንሁትን ሰጠኝ።

28 ስለዚህ እኔምለእግዚአብሔርእሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉለእግዚአብሔርየተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያለእግዚአብሔርሰገደ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *