ሳሙኤል ዳዊትን መቅባቱ
1 እግዚአብሔርሳሙኤልን፣ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው።
2 ሳሙኤል ግን፣ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ።
እግዚአብሔርምእንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፣ ‘ለእግዚአብሔርልሠዋ መጥቻለሁ’ በል።
3 እሴይን ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።”
4 ሳሙኤልእግዚአብሔርያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት።
5 ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትምለእግዚአብሔርመሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው።
6 እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ።
7 እግዚአብሔርግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና።እግዚአብሔርየሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤እግዚአብሔርግን ልብን ያያል” አለው።
8 ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንንም አልመረጠውም” አለው።
9 እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንምእግዚአብሔርአልመረጠውም” አለ።
10 እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔርእነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው።
11 ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው።
እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ።
ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው።
12 ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ።
እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።
13 ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮየእግዚአብሔርመንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።
ዳዊት ሳኦልን ማገልገሉ
14 የእግዚአብሔርመንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ከእግዚአብሔርዘንድ የታዘዘ ክፉመንፈስ ያሠቃየው ነበር።
15 የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው።
16 እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።”
17 ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።
18 ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤እግዚአብሔርምከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ።
19 ከዚያም ሳኦል፣ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ።
20 እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ፣ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው።
21 ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፣ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ።
22 ከዚያም ሳኦል፣ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ።
23 ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፣ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።