ዳዊት ለሁለተኛ ጊዜ ሳኦልን ከመግደል ታቀበ
1 የዚፍ ሰዎች ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው፣ “እነሆ፤ ዳዊት በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ተደብቆአል” ብለው ነገሩት።
2 ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፤ ከእስራኤል የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ፣ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ።
3 ሳኦልም በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ላይ በመንገድ ዳር ሰፈረ፤ ዳዊት ግን በምድረ በዳ ነበር። ዳዊትም ሳኦል እዚያ ድረስ እንደ ተከተለው ባወቀ ጊዜ፣
4 ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ።
5 ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሰራዊቱ አለቃ፣ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ሳለ፣ ሰራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6 ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፣ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው።
አቢሳም፣ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።
7 ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሰራዊቱ ወዳለበት ሄዱ። እነሆ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ጦሩም ራስጌው አጠገብ በመሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተው ነበር።
8 አቢሳም ዳዊትን፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው።
9 ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው!እግዚአብሔርበቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?
10 ሕያውእግዚአብሔርን! እግዚአብሔርራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል።
11 እግዚአብሔርበቀባው ላይ እጄን ከማንሣትእግዚአብሔርይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”
12 ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም።ከእግዚአብሔርዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና።
13 ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር።
14 ዳዊት ሰራዊቱንና የኔርን ልጅ አብኔርን፣ “አበኔር ሆይ፣ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ።
አበኔርም፣ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።
15 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው ነህ? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለምንድን ነው?
16 ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያውእግዚአብሔርን!አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤እግዚአብሔርየቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”
17 ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤
18 በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?
19 አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤እግዚአብሔርበእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፣ ቊርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣በእግዚአብሔርፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለውበእግዚአብሔርርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።
20 አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜከእግዚአብሔርፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”
21 ሳኦልም፣ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለ ከበረች፣ ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ በእርግጥ የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ፤ እጅግ ሲበዛም ተሳስቻለሁ” አለ።
22 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት።
23 እግዚአብሔርለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬእግዚአብሔርአንተን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለእግዚአብሔርበቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም።
24 እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፣ የእኔም ሕይወትበእግዚአብሔርዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”
25 ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ታላቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በእርግጥም ይከናወንልሃል” አለው።
ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ተመለሰ።