እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው
1 ብላቴናው ሳሙኤል ከዔሊ በታች ሆኖእግዚአብሔርንያገለግል ነበር። በዚያም ዘመንየእግዚአብሔርቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይታይም ነበር።
2 ዐይኖቹ ከመድከማቸው የተነሣ ማየት የተሳነው ዔሊ አንድ ሌሊት በስፍራው ተኝቶ ነበር።
3 ሳሙኤልም ደግሞ የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት፣በእግዚአብሔርቤተ መቅደስውስጥ ተኝቶ ነበር፤ የእግዚአብሔር መብራትም ገና አልጠፋም ነበር።
4 እግዚአብሔርምሳሙኤልን ጠራው።
ሳሙኤልም፣ “እነሆኝ” አለ፤
5 ወደ ዔሊም ሮጦ በመሄድ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።
ዔሊ ግን፣ “እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው፤ እርሱም ሄዶ ተኛ።
6 ደግሞምእግዚአብሔር፣ “ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው።
ሳሙኤልም ተነሣና ወደ ዔሊ ሄዶ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።
ዔሊም መልሶ፣ “ልጄ ሆይ፤ እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው።
7 በዚያም ጊዜ ሳሙኤልእግዚአብሔርንገና አላወቀም ነበር፤የእግዚአብሔርምቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።
8 እግዚአብሔርሳሙኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው፤ አሁንም ሳሙኤል ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።
ዔሊ በዚህ ጊዜ ብላቴናውን ይጠራ የነ በረውእግዚአብሔርመሆኑን ተረዳ።
9 በዚያ ጊዜ ዔሊ ሳሙኤልን፣ “ሂድና ተኛ፤ ከእንግዲህ ቢጠራህ ግን፣ ‘እግዚአብሔርሆይ፤ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር’ በል” አለው። ስለዚህም ሳሙኤል ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ።
10 እግዚአብሔርምመጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው።
ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።
11 እግዚአብሔርምሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ሁሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።
12 በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተ ሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ።
13 ዔሊ በሚያውቀው ኀጢአት ምክንያት በቤተ ሰቡ ላይ ለዘላለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር፤ ልጆቹ አስጸያፊ ነገር አድርገዋል፤ እርሱ ግን አልከለከላቸውም።
14 ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቊርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።”
15 ሳሙኤል እስኪነጋ ድረስ ተኛ፤ ከዚያም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ፤ ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ፤
16 ዔሊ ግን ሳሙኤልን፣ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ” ሲል ጠራው።
ሳሙኤልም፣ “እነሆኝ” ሲል መለሰ።
17 ዔሊም፣ “እግዚአብሔርየነገረህ ነገር ምንድ ነው? አትደብቀኝ፤ ከነገረህ ውስጥ አንዲቱን እንኳ ብትደብቀኝ እግዚአብሔር እንደዚያው ያድርግብህ፤ ከዚያ ለከፋም ይዳርግህ” አለው።
18 ስለዚህ ሳሙኤል ምንም ነገር ሳይደብቅ ሁሉንም ነገረው። ዔሊም፣ “እርሱእግዚአብሔርነው፤ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ።
19 ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤እግዚአብሔርምከእርሱ ጋር ስለ ነበረ፣ ከሚናገረው ቃል አንዳች በምድር አይወድቅም ነበር።
20 ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል በርግጥየእግዚአብሔርነቢይ መሆኑን ዐወቁ።
21 እግዚአብሔርበሴሎ ይገለጥ ነበር፤ በዚያም በቃሉ አማካይነት ራሱን ለሳሙኤል ገለጠ።