1 የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ።
ታቦቱ በፍልስጥኤማውያን ተማረከ
በዚያ ዘመን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እስራኤላውያን በአቤንኤዘር፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ።
2 ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ።
3 ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ ዛሬእግዚአብሔርበፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነንየእግዚአብሔርንየኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ።
4 ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣
በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታየእግዚእብሔርንየኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5 የእግዚአብሔርየኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ።
6 ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድ ነው?” ሲሉ ጠየቁ።
የእግዚአብሔርታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤
7 ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቶአል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም።
8 ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤
9 ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ ወንድነታችሁም ይታይ፤ ያለዚያ ባሪያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፣ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባሪያ ያደርጓችኋል። ወንድነታችሁ ይታይ፤ ተዋጉ!”
10 ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ወደቁ።
11 የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ተገደሉ።
የዔሊ መሞት
12 በዚያች ዕለት አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ፣ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ፣ ከጦሩ ሜዳ እየበረረ ወደ ሴሎ መጣ።
13 እዚያ እንደ ደረሰም፣ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ስለ ተጨነቀ፣ በመንገድ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወደ ከተማው ገብቶ የሆነውን ሁሉ ባወራ ጊዜ፣ ከተማው ሁሉ በጩኸት ተናወጠ።
14 ዔሊም ጩኸቱን በሰማ ጊዜ፣ “የምን ጩኸት ነው?” ሲል ጠየቀ።
ሰውየውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው፤
15 ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ስለ ነበር ዐይኖቹ ደክመው ማየት ተስኖአቸው ነበር።
16 ሰውየውም ዔሊን፣ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው።
ዔሊም፣ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ።
17 ወሬውን ያመጣውም ሰው፣ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሰራዊቱም ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኮአል” ብሎ መለሰለት።
18 ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፣ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፣ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅነበር።
19 በዚያን ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት፣ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት መማረክ፣ የዐማቷንና የባሏንም መሞት በሰማች ጊዜ ምጡ ስለ ጠናባት ተንበርክካ ወለደች።
20 ለመሞትም በምታጣጥርበት ጊዜ፣ በአጠገቧ የነበሩት ሴቶች፣ “አይዞሽ፤ ወንድ ልጅ ወልደሻልና በርቺ” አሏት። እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላዳመጠችም።
21 የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከ፣ ዐማቷና ባሏም ስለ ሞቱ፣ “ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድአለችው።
22 ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ተማርኮአልና ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” አለች።