ከይሁዳ የመጣ የእግዚአብሔር ሰው
1 ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣በእግዚአብሔርቃል ታዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ።
2 መሠዊያውንምበእግዚአብሔርቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህእግዚአብሔርየሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነዳል።’ ”
3 በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔርየሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈሳል’ ” የሚል ነው።
4 ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም
5 እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰውበእግዚአብሔርቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ።
6 ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደእግዚአብሔርለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰውእግዚአብሔርንለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች።
7 ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው።
8 የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም።
9 በእግዚአብሔርቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።”
10 ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ።
11 በዚያን ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት የእግዚአብሔር ሰው እዚያ ያደረገውን ሁሉና ንጉሡንም ምን እንዳለው ለአባታቸው ነገሩት።
12 አባታቸውም፣ “ለመሆኑ የተመለሰው በየትኛው መንገድ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፤ ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የተመለሰበትን መንገድ ለአባታቸው አሳዩት።
13 ስለዚህም ልጆቹን፣ “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነርሱም አህያውን ጫኑለትና ተቀምጦበት
14 እየጋለበ ያን የእግዚአብሔር ሰው ተከተለው። ከዚያም በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና፣ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።
15 ስለዚህ ነቢዩ፣ “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው።
16 የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህ ቦታም አብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤
17 ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬበእግዚአብሔርቃል ታዝዣለሁና” አለው።
18 ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክበእግዚአብሔርቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።
19 ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።
20 በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣የእግዚአብሔርቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤
21 ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔርየሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርንቃል አቃለሃል፤ አምላክህእግዚአብሔርየሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤
22 ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።
23 የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት።
24 ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር።
25 በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።
26 ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህየእግዚአብሔርንቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤እግዚአብሔርባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ።
27 ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት።
28 ከዚያም ሄዶ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ አንበሳውና አህያው በአጠገቡ ቆመው አገኘ፤ አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም አልሰበረውም።
29 ስለዚህ፣ ነቢዩ የዚያን የእግዚአብሔር ሰው ሬሳ አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነ፤ አልቅሶ ለመቅበርም ራሱ ወደሚኖርበት ከተማ አመጣው።
30 ከዚያም ሬሳውን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ “አወይ ወንድሜን” እያሉም አለቀሱለት።
31 ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እኔም በምሞትበት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ ዐጥንቶቼንም በዐጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ።
32 በቤቴል ባለው መሠዊያ፣ በሰማርያ ከተሞችና በየኰረብታው ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች ላይበእግዚአብሔርቃል ጮኾ ያሰማው መልእክት በትክክል የሚፈጸም ነውና።”
33 ይህም ሁሉ ሆኖ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ አልተመለሰም፤ ይልቁንም በኰረብታ ማምለኪያዎች ከየትኛውም ክፍል እንደ ገና ካህናትን ይሾም ጀመር፤ ካህን ለመሆን የሚፈልገውንም ሁሉ ለየኰረብታ ማምለኪያዎቹ ለየ።
34 ይህም ኀጢአት የኢዮርብዓም ቤት እንዲወድቅና ከምድር ገጽም እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ።