1 ነገሥት 2

ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው መመሪያ

1 ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ እንደ ተቃረበም፣ ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤

2 “እነሆ፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ እንግዲህ በርታ፤ ሰውም ሁን።

3 የአምላክህንየእግዚአብሔርንትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱንና ደንቦቹን ጠብቅ፤

4 እግዚአብሔርም፣ ‘ዘሮችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፣ እንዲሁም በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው በታማኝነት በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው ከዘርህ አላሳጣህም’ ሲል የሰጠኝን ተስፋ ይፈጽምልኛል።

5 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በእኔ ላይ ያደረገውን፣ እንዲሁም በእስራኤል ሰራዊት አዛዦች በኔር ልጅ በአበኔርና በዬቴሩ ልጅ በአሜሳይ ላይ የፈጸመውን አንተው ራስህ ታውቃለህ፤ ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደማቸውን አፍሶአል፤ በዚህም ደም ወገቡ ላይ የታጠቀውን ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገውን ጫማ በክሎአል።

6 መደረግ ያለበትን በጥበብህ አድርግ፤ ከነሽበቱ በሰላም ወደ መቃብርእንዲወርድ አታድርግ።

7 “ከወንድምህ ከአቤሴሎም በሸሸሁ ጊዜ መልካም ነገር አድርገውልኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ግን በጎ ነገር አድርግላቸው፤ ማእድህን ከሚካፈሉ ሰዎችም ጋር አብረው ይብሉ።

8 “ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ፣ ክፉኛ የረገመኝ የባሑሪም ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ፤ ከአንተ ዘንድ ይገኛል፤ ሊቀበለኝ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ፣ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬበእግዚአብሔርስም ምዬለታለሁ፤

9 አሁን ግን በደል እንደሌለበት ሰው አትተወው፤ ጥበበኛ ነህና መደረግ ያለበትን ታውቃለህ፤ ሽበቱን በደም ወደ መቃብር አውርድ።”

10 ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።

11 ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት ባጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።

12 ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።

የሰሎሞን መንግሥት መጽናት

13 በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤

እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።

14 ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።

እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።

15 እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩከእግዚአብሔርየተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ።

16 አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።

እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።

17 እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እምቢ አይልሽምና ሱነማዊቷን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት።

18 ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች።

19 ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጒዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።

20 እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ እሺ በለኝ” አለችው።

ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት።

21 ስለዚህም፣ “ሱነማዊቷን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው።

22 ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዊቷን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለ ሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት።

23 ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞንበእግዚአብሔርስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣እግዚአብሔርይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤

24 አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያውእግዚአብሔርንአዶንያስ ዛሬ ይሞታል!”

25 ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መቶ ገደለው።

26 ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የልዑልእግዚአብሔርንታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ አብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው።

27 ስለዚህእግዚአብሔርስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርንከእግዚአብሔርክህነት አስወገደው።

28 ከአቤሴሎም ጋር ሳይሆን ከአዶንያስ ጋር አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደእግዚአብሔርድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።

29 ኢዮአብ ወደእግዚአብሔርድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው።

30 ስለዚህም በናያስ ወደእግዚአብሔርድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው።

እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው።

በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።

31 ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን።

32 አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሎአቸዋልና ስላፈ ሰሰው ደምእግዚአብሔርይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴሩ ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከእርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ።

33 የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይየእግዚአብሔርሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።”

34 ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩተቀበረ።

35 ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ።

36 ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤

37 ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።”

38 ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።

39 ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ተብሎ ተነገረው።

40 ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጌት መልሶ አመጣቸው።

41 ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣

42 ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ ‘ወደ ሌላ ቦታ የሄድህ ዕለት እንደምትሞት ዕወቅ’ ብዬበእግዚአብሔርስም አስምዬ አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚያን ጊዜ አንተም፣ ‘መልካም ነው፤ እኔም እታዘዛለሁ’ ብለኸኝ ነበር፤

43 ታዲያለእግዚአብሔርየማልኸውን መሐላ ያልጠበቅኸውና እኔም የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልፈጸምኸው ለምንድን ነው?”

44 ንጉሡም መልሶ ሳሚን እንዲህ አለው፤ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግህበትን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ስለዚህእግዚአብሔርስለ ክፉ ሥራህ ብድሩን ይከፍልሃል።

45 ንጉሥ ሰሎሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋንበእግዚአብሔርፊት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

46 ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም ወጣ፤ ሳሚንም መቶ ገደለው።

በዚህ ጊዜም መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ ጸና።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *