የሰሎሞን ሹማምት
1 ንጉሥ ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤
2 ዋና ዋናዎቹ ሹማምቱም እነዚህ ነበሩ፤
የሳዶቅ ልጅ ዓዛርያስ፣ ካህን፤
3 የሺሻ ልጆች ኤሊሖሬፍና
አኪያ፣ ጸሓፊዎች፤
የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፣ ታሪክ ጸሓፊ፤
4 የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ የሰራዊቱ ዋና አዛዥ፤
ሳዶቅና አብያታር፣ ካህናት፤
5 የናታን ልጅ ዓዛርያስ፣ የአውራጃ
ገዦች የበላይ ኀላፊ፤
የናታን ልጅ ዛቡድ፣ ካህንና የንጉሡ
የቅርብ አማካሪ፤
6 አሒሳር፣ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፤
የዓብዳ ልጅ አዶኒራም የግዳጅ ሥራ
ተቈጣጣሪ።
7 እንዲሁም ሰሎሞን ለንጉሡና ለንጉሡ ቤት የሚሆነውን ቀለብ ከመላው እስራኤል የሚሰበስቡ ዐሥራ ሁለት የአውራጃ ገዦች ነበሩት፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው በዓመት ውስጥ የወር ቀለብ የሚያቀርቡ ነበሩ።
8 ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፤
ቤንሑር፣ በኰረብታማው በኤፍሬም
ምድር፤
9 ቤንጼቄር፣ በማቃጽ፣ በሻዓልቢም፣
በቤትሳሜስ፣ በኤሎንቤትሐናን፤
10 ቤንሔሴድ፣ በአሩቦት ውስጥ
የሚገኙት ሰኰትና የኦፌር አገር
በሙሉ የእርሱ ነበር፤
11 ቤን አሚናዳብ፤ በናፎትረ ዶር፣
እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን
አግብቶ የነበረ ነው፤
12 የአሒሉድ ልጅ በዓና፣ በታዕናክና
በመጊዶ እንዲሁም ከጻርታን ቀጥሎ
ቍልቍል እስከ ኢይዝራኤል ባለው
በቤትሳን ሁሉ፣ ከዚያም ዮቅምዓምን
ተሻግሮ እስከ አቤልምሖላና ድረስ፣
13 ቤንጌበር፣ በገለዓድ ራሞት ከተማ
እዚያው ገለዓድ ውስጥ የምናሴ
ልጅ የኢያዕር መንደሮች፣ በባሳንም
የአርጎብ አውራጃ እንዲሁም በሮቻ
ቸው የናስ መወርወሪያ በሆኑ ሥልሳ
ባለ ቅጥር ታላላቅ ከተሞች፤
14 የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤ በማሃናይም፣
15 አኪማአስ በንፍታሌም፣ እርሱም
የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ
የነበረ ነው፤
16 የኩሲ ልጅ በዓና፤ በአሴርና በበዓሎት፣
17 የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሳኮር፣
18 የኤላ ልጅ ሳሚ በብንያም፣
19 የኡሪ ልጅ ጌበር፤
በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣
በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፣ እርሱም
የአውራጃው ብቸኛ ገዥ ነበር።
ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለት ቀለብ
20 የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሆነ፤ ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር።
21 ሰሎሞንም ከወንዙአንሥቶ እስከ ፍልስጥኤማውያን ምድር፣ ከዚያም እስከ ግብፅ ዳርቻ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ገዛ፤ እነዚህም አገሮች ግብር አመጡለት፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ተገዙለት።
22 ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለትም ቀለብ ይህ ነበር፤ ሠላሳ ኮርማለፊያ ዱቄት፣ ሥልሳ ኮርመናኛ ዱቄት፣
23 ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ።
24 ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር።
25 በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ።
26 ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺህ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶችነበሩት።
27 የየአውራጃው ሹማምትም በየወር ተራቸው ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ማእድ የሚቀርቡትን ሁሉ ምንም ሳያጓድሉ ይቀልቡ ነበር፤
28 እንዲሁም ለሠረገላ ፈረሶችና ለፈጣን ፈረሶች የተመደበውን ገብስና ጭድ ከተፈለገው ቦታ ድረስ ያመጡ ነበር።
የሰሎሞን ጥበብ
29 አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው።
30 የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤
31 እርሱም ከማንም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፣ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታን፣ ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ደግሞም ከደራል ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ ተሰማ።
32 እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺህ አምስት ነበር።
33 ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሮአል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በሆዳቸው ስለሚሳቡ እንስሳትና ስለ ዓሦችም ተናግሮአል፤
34 ጥበቡን ከሰሙት ከዓለም ነገሥታት ሁሉ የተላኩ፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለማድመጥ መጡ።