1 ዜና መዋዕል 13

የታቦቱ መመለስ

1 ዳዊትም ሻለቆችና መቶ አለቆች ከሆኑት የጦር ሹማምቱ ሁሉ ጋር ተማከረ።

2 ከዚያም ለመላው የእስራኤል ማኅበር እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና የአምላካችንየእግዚአብሔርፈቃድ ከሆነ፣ በእስራኤል ግዛት ሁሉ ለሚኖሩ በሩቅም ሆነ በቅርብ ላሉት ለቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም በየራሳቸው ከተሞችና መሰማሪያዎች የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን መጥተው ከእኛ ጋር እንዲሰባሰቡ እንላክባቸው።

3 በሳኦል ዘመነ መንግሥት ሳንፈልገውየነበረውን የአምላካችንን ታቦት መልሰን ወደ እኛ እናምጣ”።

4 ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ መላው ማኅበር ይህንኑ ለማድረግ ተስማማ።

5 ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ለማምጣት ከግብፅ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መተላለፊያድረስ የሰፈሩትን እስራኤላውያን ሁሉ ሰበሰበ።

6 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን፣የእግዚአብሔርአምላክን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደተባለችው ወደ በኣላ ሄዱ።

7 የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ላይ አድርገው አመጡት፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም ዖዛና አሒዮ ነበሩ።

8 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆና በከበሮ፣ በጸናጽልና በመለከት በሙሉ ኀይላቸው በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር።

9 ወደ ኪዶን ዐውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ አደናቅፏቸው ስለ ነበር፣ ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ እጁን ዘረጋ።

10 ታቦቱን በእጁ ስለ ነካ፣የእግዚአብሔርቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።

11 የእግዚአብሔርቍጣ ዖዛን በድንገት ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የዖዛ ስብራትተብሎ ይጠራል።

12 ዳዊት በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት ማምጣት እችላለሁ?” አለ።

13 ስለዚህ ታቦቱን ወደ ዳዊት ከተማ በመውሰድ ፈንታ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው።

14 የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤት ከቤተ ሰቡ ጋር ሦስት ወር ተቀመጠ፤እግዚአብሔርምቤተ ሰቡንና ያለውንም ሁሉ ባረከ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *