1 ዜና መዋዕል 20

የራባ ከተማ መያዝ

1 ነገሥታት ለጦርነት በሚሄዱበት በጸደይ ወራት፣ ኢዮአብ የጦር ሰራዊቱን እየመራ ሄዶ የአሞናውያንን አገር አጠፋ፤ ወደ ራባትም ሄዶ ከበባት፤ ዳዊት ግን ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። ኢዮአብም ራባትን ወግቶ አፈራረሳት፤

2 ዳዊት የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊትወርቅ ነበረ፤ ይህንንም በዳዊት ራስ ላይ ጫኑለት፤ እንዲሁም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ።

3 በዚያ የነበረውንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ ዶማና መጥረቢያ ይዘው እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊት በሌሎቹም የአሞን ከተሞች ሁሉ ይህንኑ አደረጉ። ከዚያም ዳዊትና መላው ሰራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከፍልስጥኤማውያን ጋር የተደረገ ጦርነት

4 ከዚያም በኋላ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በጌዝር ጦርነት ተደረገ፤ በዚያ ጊዜ ኩሳታዊው ሴቦካይ የራፋይም ዘር የሆነውን ሲፋይን ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ድል ተመቱ።

5 ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ፤ የያዒር ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ ውፍረቱ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሚያህለውን የጌት ተወላጅ የሆነውን የጎልያድን ወንድም ላሕሚን ገደለ።

6 ደግሞም ጌት ላይ በተደረገ ሌላ ጦርነት፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣት በድምሩ ሃያ አራት ጣት የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ ይህም እንደዚሁ ከራፋይም ዘር ነበረ።

7 እርሱም እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።

8 በጌት የነበሩ የራፋይም ዘሮች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *