2 ሳሙኤል 12

ናታን ዳዊትን ገሠጸው

1 እግዚአብሔርናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ።

2 ባለ ጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤

3 ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች።

4 ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።

5 ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያውእግዚአብሔርንይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!

6 እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለ ማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።”

7 ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርየሚለው ይህን ነው፤ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤

8 የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር።

9 ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣የእግዚአብሔርንቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው።

10 ስለዚህ ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም፤ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና።’

11 “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።

12 አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።’ ”

13 ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርንበጣም በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔርኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤

14 ይህን በመፈጸምህ ግን፣የእግዚአብሔርጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉትስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”

15 ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፣ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃንእግዚአብሔርከባድ ሕመም ላይ ጣለው።

16 ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ በተከታታይ ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ።

17 የቤተ ሰው ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያስነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ነገር አልበላም።

18 በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፣ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጒዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ።

19 ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፣ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “አዎን ሞቶአል” ብለው መለሱለት።

20 በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደእግዚአብሔርምቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ።

21 አገልጋዮቹም፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት።

22 እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፣ ‘እግዚአብሔርይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ።

23 አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፣ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፣ እርሱ ወደ እኔ አይመለስ!”

24 ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው።እግዚአብሔርምወደደው፤

25 እግዚአብሔርሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ።

26 በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ረባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ።

27 ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ረባትን ወግቼ የውሃውን ከተማ ይዤአለሁ፤

28 እንግዲህ የቀረውን ሰራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ ያለበለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።”

29 ስለዚህ ዳዊት መላውን ሰራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት በመሄድ ወግቶ ያዛት።

30 የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት የሚመዝን አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን፣ በከበረ ዕንቊም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤

31 እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ የብረት መቈፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፣ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በሌሎቹ የአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሰራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *