የዳዊት የምስጋና መዝሙር
1 እግዚአብሔርከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦልም እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃልለእግዚአብሔርዘመረ፤
2 እንዲህም አለ፤
“እግዚአብሔርዐለቴ ዐምባዬና ታዳጊዬ ነው፤
3 አምላኬ፣ የምጠጋበት ዐለቴ፣
ጋሻዬና የድነቴ ቀንድነው።
እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊያና አዳኜ ነው፤
ከኀይለኞች ሰዎች ታድነኛለህ።
4 ምስጋና የሚገባውንእግዚአብሔርን
እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
5 “የሞት ማዕበል ከበበኝ፤
የጥፋትም ጐርፍ አሰጠመኝ።
6 የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤
የሞትም ወጥመድ ተጋረጠብኝ።
7 በጨነቀኝ ጊዜእግዚአብሔርንጠራሁት፤
ወደ አምላኬም ጮኽሁ።
እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤
ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ።
8 “ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤
የሰማያትም መሠረቶችተናጉ፤
እርሱ ተቈጥቶአልና ራዱ።
9 ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤
ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤
ከውስጡም ፍሙ ጋለ።
10 ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤
ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
11 በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤
በነፋስም ክንፍ መጠቀ።
12 ጨለማው በዙሪያው እንዲከበው፣
ጥቅጥቅ ያለውም የሰማይ ዝናም ደመና እንዲሰውረው አደረገ።
13 በእርሱ ፊት ካለው ብርሃን፣
የመብረቅ ብልጭታ ወጣ።
14 እግዚአብሔርከሰማያት አንጐደጐደ፤
የልዑልም ድምፅ አስተጋባ።
15 ፍላጻውን ሰድዶ ጠላቶቹን በተናቸው፤
መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው።
16 ከእግዚአብሔርተግሣጽ፣ ከአፍንጫው
ከሚወጣው፣ ከእስትንፋሱ ቍጣ የተነሣ፣
የባሕር ሸለቆዎች ታዩ፤ የምድር
መሠረቶችም ተገለጡ።
17 “ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤
ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ።
18 ከብርቱ ጠላቶቼ፣
ከማልቋቋማቸውም ባለጋሮቼ ታደገኝ።
19 በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤
እግዚአብሔርግን ደገፈኝ።
20 ሰፊ ወደ ሆነ ስፍራ አወጣኝ፤
በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ።
21 “እግዚአብሔርእንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤
እንደ እጄም ንጹሕነት ብድራትን ከፈለኝ፤
22 የእግዚአብሔርንመንገድ ጠብቄአለሁና፤
ከአምላኬም ዘወር ብዬ ክፉ ነገር አላደረግሁም።
23 ሕጉ ሁሉ በፊቴ ነው፤
ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም።
24 በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤
ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።
25 እግዚአብሔርእንደ ጽድቄ፣
በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕናብድራትን ከፈለኝ።
26 “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን፣
ለቅን ሰው አንተም ቅን መሆንህን ታሳያለህ።
27 ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣
ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ።
28 አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤
ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል።
29 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤
እግዚአብሔርምጨለማዬን ያበራል።
30 በአንተ ርዳታ በጠላት ሰራዊት ላይ ወደ
ፊት ገፍቼ እሄዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥሩን እዘላለሁ።
31 “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤
የእግዚአብሔርምቃል የነጠረ ነው፤
ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤
32 ከእግዚአብሔርበቀር አምላክ ማን አለና፤
ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው?
33 ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣
መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው።
34 እግሮቼን እንደ ብሆር እግር ያበረታል፤
በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል።
35 እጆቼን ለጦርነት ያሰለጥናል፤
ክንዶቼም የናስ ቀስት ይገትራሉ።
36 የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤
ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል።
37 እርምጃዬን አሰፋህ፤
እግሮቼም አልተሰነካከሉም።
38 “ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤
እስኪደመሰሱም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም።
39 ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ ተመልሰውም መቆም አልቻሉም፤
ከእግሬም ሥር ወድቀዋል።
40 ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፣
ተቃዋሚዎቼንም ከእግሬ ሥር አንበረከካቸው።
41 ጠላቶቼ ፊታቸውን አዙረው እንዲሸሹ አደረግሃቸው።
ባላንጣዎቼንም ደመሰስኋቸው።
42 ለርዳታ ጮኹ፤ ያዳናቸው ግን አልነበረም፤ ወደእግዚአብሔርጮኹ፤ እርሱ ግን
አልመለሰላቸውም።
43 በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አድቅቄ ፈጨዃቸው፤
በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም።
44 “በሕዝቤ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤
የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ።
የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤
45 ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤
እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል።
46 ባዕዳን ፈሩ፤
ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ።
47 “እግዚአብሔርሕያው ነው፤ ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤
የድነቴ ዐለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል።
48 የሚበቀልልኝ አምላክ፣
መንግሥታትንም ከሥሬ የሚያስገዛልኝ እርሱ ነው፤
49 እርሱ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ ያወጣኛል።
አንተ ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤
ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ።
50 ስለዚህእግዚአብሔርሆይ፤
በመንግሥታት መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ።
51 ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤
ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፣
ለዘላለም የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳየዋል።”