2 ሳሙኤል 5

ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ

1 የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤

2 ባለፈው ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረ ጊዜ፣ እስራኤልን በጦርነት የምትመራቸው አንተ ነበርህ፤እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”

3 ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይበእግዚአብሔርፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።

4 ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ።

5 በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።

ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ

6 ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት።

7 ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት።

8 በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶችወደሚሆኑ፣ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያውሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።

9 ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት።

10 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ።

11 በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት።

12 እግዚአብሔርበእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ።

13 ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ሌሎች ቁባቶች አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።

14 በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣

15 ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣

16 ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።

ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ

17 ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ለመፈለግ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ።

18 በዚህ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ።

19 ስለዚህም ዳዊትእግዚአብሔርን፣ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸው? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?” ሲል ጠየቀ።

እግዚአብሔርም፣“አዎን ሂድ፤ በእርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።

20 ስለዚህም ዳዊት ወደ በአልፐራሲምሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣እግዚአብሔርምጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም በአልፐራሲም ተባለ።

21 ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው።

22 ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ።

23 ስለዚህም ዳዊትእግዚአብሔርንጠየቀ፤እግዚአብሔርምእንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በበለሳኑ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤

24 በበለሳኑ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጒዞ ድምፅ ስትሰማም፣እግዚአብሔርየፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቶአል ማለት ነውና በዚያን ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።”

25 ስለዚህም ዳዊትእግዚአብሔርእንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖንእስከ ጌዝር ድረስ እያሳደደ መታቸው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *