2 ነገሥት 11

ጎቶልያና ኢዮአስ

1 የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን በሰማች ጊዜ፣ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች።

2 የንጉሥ ኢዮራም ልጅ፣ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት ግን የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሊገደሉ ከነበሩት ልዑላን መካከል ሰርቃ ወሰደችው። እንዳይገድሉትም ከጎቶልያ በመደበቅ እርሱንና ሞግዚቱን በአንድ እልፍኝ ሸሸገቻቸው።

3 ጎቶልያ አገሩን በምትገዛበት ጊዜም ከሞግዚቱ ጋር ስድስት ዓመትበእግዚአብሔርቤት ተሸሸገ።

4 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን በማድረግበእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።

5 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤

6 ሌላው ከሦስት አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ።

7 እናንተ እንደተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን ቤተ መቅደስ ጠብቁ።

8 ሁላችሁም መሣሪያችሁን ይዛችሁ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ቢኖርግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ አትለዩት።”

9 የመቶ አለቆቹም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።

10 ካህኑምበእግዚአብሔርቤት የነበረውን የንጉሥ ዳዊትን ጦርና ጋሻ ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።

11 ወታደሮቹም እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን ይዘው፣ ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።

12 ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጠው፣ መንገሡን ዐወጀ፤ ኢዮአስም ተቀብቶ ነገሠ። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።

13 ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደች።

14 እነሆ፤ በወጒ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀዳ፣ “ይህ ክዳት ነው! ክዳት ነው!” በማለት ጮኸች።

15 ካህኑ ዮዳሄም ጭፍሮቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ በሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔርቤት መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር።

16 ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት ስፍራ ስትደርስ፣ ይዘው እዚያው ገደሏት።

17 ዮዳሄምየእግዚአብሔርሕዝብ ይሆኑ ዘንድበእግዚአብሔርናበንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ።

18 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ሄደው አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።

ከዚያም ካህኑ ዮዳሄየእግዚአብሔርንቤተ መቅደስ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ።

19 ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ ካራውያንንና ዘበኞቹን እንዲሁም የአገሩን ሕዝብ በሙሉ በመያዝ ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ንጉሡንከእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ወስደው በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ታች ወዳለው ቤተ መንግሥት ይዘውት ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤

20 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አለው፤ ጎቶልያ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሰይፍ ተገድላ ስለ ነበር፣ ከተማዪቱ ጸጥ አለች።

21 ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *