2 ነገሥት 12

ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን አደሰ

1 ኢዩ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ ነገሠ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች፤ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች።

2 ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስበእግዚአብሔርፊት መልካም ነገር አደረገ።

3 ይሁን እንጂ የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በእነዚህ ቦታዎች መሠዋቱንና ማጠኑን እንደ ቀጠለ ነበር።

4 ኢዮአስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለቤተ መቅደሱ የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ።

5 እያንዳንዱም ካህን ገንዘቡን ከገንዘብ ያዡ እጅ ይቀበል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል።”

6 ይሁን እንጂ እስከ ሃያ ሦስተኛው የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን አላደሱም ነበር።

7 ስለዚህ ኢዮአስ ካህኑን ዮዳሄንና ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ፣ “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ያላደሳችሁት ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ ቀጥሎም፣ “ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል እንጂ ከገንዘብ ያዦች አትቀበሉ” አላቸው።

8 ካህናቱም ከእንግዲህ ከሕዝቡ ገንዘብ ላለመሰብሰብና ቤተ መቅደሱንም ራሳቸው ላለማደስ ተስማሙ።

9 ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀለት፤ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ በሚያስገባው በስተ ቀኝ በኩል በመሠዊያው አጠገብ አኖረው። በራፉን የሚጠብቁት ካህናትም ወደእግዚአብሔርቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡ ነበር።

10 በሣጥኑም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ ቈጥረው በየከረጢቱ በማስገባት ቋጥረው ያኖሩት ነበር።

11 የገንዘቡ ልክም ተመዝኖ ከታወቀ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን ያስረክቧቸዋል፤ ይህምየእግዚአብሔርንቤተ መቅደስ ለሚሠሩ አናጢዎችና ግንበኞች፣

12 ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለድንጋይ ቅርጽ አውጭዎች የሚከፈል እንዲሁምየእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ለሚታደስበት ዕንጨትና ጥርብ ድንጋይ መግዣ የሚውል ነበር።

13 ለቤተ መቅደሱ ከገባው ገንዘብ ግንለእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ግልጋሎት ለሚውሉ የብር ጽዋዎች፣ መኰስተሪያዎች፣ ድስቶች፣ መለከቶችና ወይም ለሌሎች የወርቅም ሆነ የብር ዕቃዎች መሥሪያ አልዋለም፤

14 የተከፈለው ግን ቤተ መቅደሱን ለሚያድሱ ሠራተኞች ብቻ ነበር።

15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘቡ የተሰጣቸው ሰዎች ፍጹም ታማኞች በመሆናቸው ተቈጣጣሪ ማድረግ አላስፈለጋቸውም ነበር።

16 ስለ በደል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ገንዘብ ግን የካህናቱ በመሆኑ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ አይገባም ነበር።

17 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጣ፤ ጌትንም አደጋ ጥሎ ያዛት። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ፊቱን አዞረ።

18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ግን አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮሆራም፣ አካዝያስለእግዚአብሔርቀድሰው የለዩአቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ፣ እርሱ ራሱ የቀደሳቸው ስጦታዎች እንዲሁምበእግዚአብሔርቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ሰብስቦ ለሶርያ ንጉሥ ለአዛሄል ላከለት፤ አዛሄልም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።

19 ኢዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመው ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

20 ሹማምቱም በእርሱ ላይ ዐመፁበት፤ ቊልቊል ወደ ሲላ በሚወስደው መንገድ ላይ በቤት ሚሎ ገደሉት።

21 ገዳዮቹ ሹማምትም የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ነበሩ። እርሱም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አሜስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *