ሆሴዕ የመጨረሻው የእስራኤል ንጉሥ
1 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዘጠኝ ዓመትም ገዛ።
2 እርሱምበእግዚአብሔርፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ክፉ ሥራው ግን ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያህል አልነበረም።
3 የአሦር ንጉሥ ሰልም ናሶር ሊወጋው መጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ገበረለትም።
4 የአሦር ንጉሥ ግን ሆሴዕ እንደ ከዳው ተገነዘበ፤ ምክንያቱም ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሲጎር መልክተኞች ስለላከና በያመቱም ያደርግ እንደ ነበረው ለአሦር ንጉሥ ስላልገበረ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ስልምናሶር ይዞ ወህኒ ቤት አስገባው።
5 የአሦርም ንጉሥ አገሩን በሙሉ ወረረ፤ ወደ ሰማርያም ገሥግሦ ሦስት ዓመት ከበባት።
6 በሆሴዕ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው። እነዚህም በአላሔ፣ ጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብ እንዲሁም በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።
እስራኤላውያን በኀጢአታቸው ምክንያት ተማረኩ
7 እንግዲህ እስራኤላውያን ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው፣ ከግብፅ ምድር ከፈርዖን አገዛዝ ከግብፅ ንጉሥ ያወጣቸውን አምላካቸውንእግዚአብሔርንስለ በደሉት ነው፤ እንዲሁም ሌሎች አማልክትን በማምለክ፣
8 እግዚአብሔርከፊታቸው አሳዶ ያወጣቸውን የአሕዛብንና የእስራኤልም ነገሥታት ወደ ምድሪቱ ያገቡትን አጸያፊ ልማድ ስለ ተከተሉ ነበር።
9 እስራኤላውያን በአምላካቸውበእግዚአብሔርላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ።
10 በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ።
11 እግዚአብሔርከፊታቸው አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤እግዚአብሔርንምየሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ።
12 እግዚአብሔር፣ “ይህን ማድረግ አይገባችሁም”ቢላቸውም እንኳ እነርሱ ጣዖታትን አመለኩ።
13 ይህም ሆኖእግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለ ራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
14 ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤እግዚአብሔርአምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።
15 ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤እግዚአብሔርእንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።
16 አምላካቸውእግዚአብሔርያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤
17 እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።ጥንቈላና መተት አደረጉ፤በእግዚአብሔርምፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቊጣም አነሣሡት።
18 ስለዚህእግዚአብሔርበእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ።
19 ይሁዳም ቢሆን ከእስራኤል የተቀበለውን ልማድ ተከተለ እንጂ የአምላኩንየእግዚአብሔርንትእዛዝ አልጠበቀም።
20 ስለዚህእግዚአብሔርየእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ተዋቸው፤ አስጨነቃቸው፤ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸውም ድረስ በማራኪዎቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
21 እስራኤልን ከዳዊት ቤት ከለየ በኋላ፣ እነርሱ የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እስራኤልእግዚአብሔርንእንዳይከተል በማሳት ትልቅ ኀጢአት እንዲሠራ አደረገ።
22 እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም።
23 እግዚአብሔርበባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል።
አሦራውያን በሰማርያ ሰፈሩ
24 የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር።
25 በዚያ መኖር እንደ ጀመሩምእግዚአብሔርንአላመለኩም፤ ስለዚህእግዚአብሔርአንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ።
26 ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣእግዚአብሔርሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው።
27 ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በእዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ።
28 ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶእግዚአብሔርንእንዴት ማምለክ እንደሚገባቸው አስተማራቸው።
29 ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ።
30 ከባቢሎን የመጡት ሱኮትበኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አስማትን ሠሩ፤
31 አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።
32 እግዚአብሔርንአመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ።
33 በአንድ በኩልእግዚአብሔርንሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።
34 ይህንንም ልማዳቸውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተውትም፤እግዚአብሔርንበአግባቡ አያመልኩም፤ እንዲሁም እስራኤል ብሎ ለጠራው ለያዕቆብ ዘሮች የሰጣቸውን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞችን አይከተሉም።
35 እግዚአብሔርከእስራኤላውያን ጋር ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አታምልኳቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠውላቸውም፤
36 ማምለክ የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁንእግዚአብሔርንብቻ ነው። ለእርሱ ስገዱ፤ ለእርሱም መሥዋዕት አቅርቡ።
37 የጻፈላችሁን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ምንጊዜም ተግታችሁ ጠብቁ። ሌሎች አማልክትን አታምልኩ።
38 ከእናንተ ጋር የገባሁትን ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትም አታምልኩ።
39 ይልቅስ አምላካችሁንእግዚአብሔርንአምልኩ፤ ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እርሱ ነውና።”
40 ነገር ግን በቀደመው ልማዳቸው ጸኑ እንጂ አልተመለሱም።
41 እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳ በአንድ ወገንእግዚአብሔርንቢያመልኩት የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው ያደረጉትን ዛሬም እንደ ቀጠሉበት ነው።