የሕዝቅያስ መታመም
1 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እግዚአብሔር፣ ‘ትሞታለህ ከእንግዲህ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል’ ብሎሃል” አለው።
2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደእግዚአብሔርጸለየ፤
3 “እግዚአብሔርሆይ፤ በታማኝነትና በፍጹም ልብ በፊትህ እንደሄድሁ፣ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ አስብ፤” ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።
4 ኢሳይያስ የመካከለኛውን አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊትየእግዚአብሔርቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤
5 “ተመለስና የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ እፈውስሃለሁ። ከዛሬ ሦስት ቀን በኋላ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤
6 በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔ ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።’ ”
7 ከዚያም ኢሳይያስ፣ “ትኵስ የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጁ” አላቸው፤ እነርሱም አዘጋጅተው ዕባጩ ላይ አደረጉለት፤ ተፈወሰም።
8 ሕዝቅያስም፣ “እግዚአብሔርእኔን ስለ መፈወሱ፣ ከሦስት ቀን በኋላም ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ስለ መውጣቴ ምልክቱ ምንድን ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀው።
9 ኢሳይያስም፣ “እግዚአብሔርየሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ምልክቱ ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይቅደምን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ?” ሲል ጠየቀው።
10 ሕዝቅያስም መልሶ፣ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ ይልቁን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ” አለ።
11 ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደእግዚአብሔርጮኸ፤እግዚአብሔርምአካዝ በሠራው ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው እንዲመለስ አደረገ።
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
12 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመም ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ገጸ በረከት ለሕዝቅያስ ላከለት።
13 ሕዝቅያስም መልክተኞቹን ተቀብሎ በዕቃ ቤቱ ያለውን ሁሉ ብሩን፣ ወርቁን ቅመማ ቅመሙንና ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ዘይት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱንና በቀረውም ግምጃ ቤት ያለውን በሙሉ አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በመላው ግዛቱ ሕዝቅያስ ሳያሳያቸው የቀረ ምንም ነገር አልነበረም።
14 ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? የመጡትስ ከወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።
ሕዝቅያስም መልሶ፣ “የመጡት ከሩቅ አገር ከባቢሎን ነው” አለው።
15 ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ምን ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።
ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በግምጃ ቤቶቼ ሳላሳያቸው የቀረ ምንም ነገር የለም” አለ።
16 ከዚያም ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርንቃል ስማ፤
17 በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት በሙሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በርግጥ ይመጣል፤ አንዳች የሚቀር ነገር የለም ይላልእግዚአብሔር።
18 የሥጋህ ቁራጭ የዐጥንትህ ፍላጭ ከሚሆኑት፣ ከምትወልዳቸው ልጆችህ አንዳንዶቹ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎንም ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ይሆናሉ።”
19 ሕዝቅያስም፣ “የተናገርኸውየእግዚአብሔርቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ፤ “እኔ እስካለሁ ድረስ ሰላምና ጸጥታ ከተገኘ የሆነው ይሁን” ብሎ አስቦአልና።
20 በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ ኵሬውንና ውሃውን ወደ ከተማዪቱ ያመጣበትን የመሬት ለመሬት ቦይ እንዴት አድርጎ እንደ ሠራው በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
21 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።