የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
1 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱምበእግዚአብሔርፊት ቅን ነገር እንዳደረገው እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።
2 በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በኣሊምን ለማምለክም የተቀረጹ ጣዖታትን ሠራ።
3 እግዚአብሔርከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን አሕዛብ ልማድ በመከተል፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ዐጠነ፤ ወንዶች ልጆቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
4 በኰረብታ መስገጃዎችና በተራሮች አናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።
5 ስለዚህአምላኩእግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ አልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጒዳት አደረሰበት።
6 ይሁዳ የአባቶቹንአምላክእግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ወታደሮች ገደለ።
7 ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
8 እስራኤላውያንም ከገዛ ወገኖቻቸው ሁለት መቶ ሺ ባለ ትዳር ሴቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
9 ዖዴድ የተባለየእግዚአብሔርነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁአምላክእግዚአብሔር ይሁዳን ስለተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቊጣ ፈጃችኋቸው።
10 አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁአምላካችሁንእግዚአብሔርን አልበደላችሁምን?
11 እንግዲህ ስሙኝ፤የእግዚአብሔርአስፈሪ ቊጣ በእናንተ ላይ ነዶአልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”
12 ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣
13 “እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ ያለዚያ እኛበእግዚአብሔርፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቶአል፤ ቊጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።
14 ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ።
15 በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቁታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16 በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤
17 ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና።
18 ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢአቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም።
19 የእስራኤልንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስ ፋፋናለእግዚአብሔርምየነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣እግዚአብሔርይሁዳን አዋረደ።
20 የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም።
21 አካዝከእግዚአብሔርቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።
22 ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ለእግዚአብሔርየነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤
23 እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ።
24 አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ፤የእግዚአብሔርንቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማዕዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።
25 በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹንአምላክእግዚአብሔርን ለቊጣ አነሣሣው።
26 በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና አካሄዱ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
27 አካዝ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በኢየሩሳሌምም ከተማ ተቀበረ፤ የተቀበረው ግን በእስራኤል ነገሥታት መካነ መቃብር አልነበረም። ልጁ ሕዝቅያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።