2 ዜና መዋዕል 33

የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ

1 ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ።

2 እግዚአብሔርከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸውን ሕዝቦች አስጸያፊ ልማድ በመከተልምበእግዚአብሔርፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

3 አባቱ ሕዝቅያስ ያጠፋቸውን የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበአሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሰገደ፤ አመለካቸውም።

4 እግዚአብሔር፣“ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበትበእግዚአብሔርቤተ መቀደስ መሠዊያዎችን ሠራ።

5 በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ።

6 በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቊጣ ያነሣሣው ዘንድበእግዚአብሔርፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።

7 ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤

8 በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕግጋቴን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር የእስራኤላውያን እግር ከእንግዲህ ለቆ እንዲወጣ አላደርግም።”

9 ምናሴ ግንእግዚአብሔርበእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ።

10 እግዚአብሔርለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።

11 ስለዚህእግዚአብሔርየአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

12 በተጨነቀም ጊዜየአምላኩንየእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።

13 ወደ እርሱም በጸለየ ጊዜ፣ በጭንቀት ልመናው ራርቶለትእግዚአብሔርጸሎቱን ሰማው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው፤ ምናሴምእግዚአብሔርአምላክ መሆኑን ዐወቀ።

14 ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው ከግዮን ምንጭ ምዕራብ አንሥቶ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ያለውን የዳዊትን ከተማ የውጭውን ቅጥር፣ የዖፊልን ኰረብታ እንዲከብ በማድረግ፣ ይበልጥ ከፍ አድርጎ እንደ ገና ሠራው። በተመሸጉትም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጦር አዛዦችን አኖረ።

15 እንግዶች አማልክትንና ጣዖታቱንከእግዚአብሔርቤተ መቅደስ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ኰረብታና በኢየሩሳሌም የሠራቸውንም መሠዊያዎች ሁሉ አራቀ፤ ከከተማዪቱም ውጭ ጣላቸው።

16 ከዚያምየእግዚአብሔርንመሠዊያ ዐደሰ፤ በላዩም የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይሁዳም የእስራኤልንአምላክእግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አዘዘ።

17 ሕዝቡ ግን በኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መሠዋቱን ቢቀጥልም፣ የሚሠዋው ግን ለአንዱአምላክለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።

18 በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ወደ አምላኩ ያቀረበው ጸሎቱና ባለ ራእዮች በእስራኤልአምላክበእግዚአብሔር ስም የነገሩት ቃል በእስራኤልነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

19 ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጒደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለ ራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል።

20 ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሞን

21 አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሁለት ዓመት ገዛ።

22 አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱምበእግዚአብሔርፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ አሞንም ምናሴ ያሠራቸውን ጣዖታት ሁሉ አመለከ፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።

23 አሞንበእግዚአብሔርፊት ራሱን እንዳዋረደ እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ።

24 የአሞን ሹማምት በእርሱ ላይ አሢረው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት።

25 ከዚያም ያገሩ ሕዝብ በንጉሡ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእርሱ ፈንታ አነገሡት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *