የቤተ መቅደሱ መመረቅ
1 ሰሎሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በላ፤የእግዚአብሔርምክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው።
2 የእግዚአብሔርክብርየእግዚአብሔርንቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ ወደዚያ መግባት አልቻሉም።
3 እስራኤላውያንም ሁሉ እሳቱ ሲወርድ፣የእግዚአብሔርንምክብር ከቤተ መቅደሱ በላይ ሲያዩ፣ በመተላለፊያው ወለል ላይ ተንበረከኩ፤ በግንባራቸውም ወደ መሬት ተደፍተው ሰገዱ፤ እንዲህ እያሉምለእግዚአብሔርምስጋና አቀረቡ፤
“እርሱ ቸር ነውና፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
እያሉምእግዚአብሔርንአመሰገኑ።
4 ከዚህ በኋላ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉበእግዚአብሔርፊት መሥዋዕት አቀረቡ።
5 ንጉሥ ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺህ በግና ፍየል ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ።
6 ካህናቱም እንደ ሌዋውያኑ፣ ንጉሥ ዳዊትእግዚአብሔርእንዲወደስበት የሠራውንና “ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለትእግዚአብሔርንባመሰገነ ጊዜ የተቀመጠበትንየእግዚአብሔርንየዜማ መሣሪያ ይዘው በተመደበላቸው ስፍራ ቆሙ። ካህናቱ በሌዋውያኑ ትይዩ ሆነው መለከቶቻቸውን ሲነፉም እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር።
7 ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን ቊርባንና ስቡን መያዝ ስላልቻሉከእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የመካከለኛውን አደባባይ ክፍል ቀድሰው፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱንስብ በዚያ አቃጠለ።
8 በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር።
9 መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።
10 ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡምእግዚአብሔርለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ በልባቸው ደስ እያላቸውና ሐሤት እያደረጉ ሄዱ።
እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገለጠለት
11 ሰሎሞንየእግዚአብሔርንቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ጨረሰ፤ለእግዚአብሔርቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣
12 እግዚአብሔርበሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤
“ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንንም ስፍራ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።
13 “ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድበት ጊዜ፣
14 በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።
15 አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ።
16 ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሸዋለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
17 “አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕግጋቴን ብትጠብቅ፣
18 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘ከዘርህ እስራኤልን የሚገዛ አታጣም’ ብዬ በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።
19 “እናንተ ግን እኔን ከመከተል ተመልሳችሁ የሰጠኋችሁን ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትተው፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኩ፣
20 በዚያን ጊዜ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፤ በሕዝቦችም ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ አደርገዋለሁ።
21 ይህ ቤተ መቅደስ አሁን እጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም በአጠገቡ የሚያልፉ ሁሉ በመገረም፤ ‘እግዚአብሔርበዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያመጣው ከቶ ለምን ይሆን?’ ይላሉ፤
22 ሕዝቡም፣ ‘ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውንአምላክእግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፣ ስላመለኳቸውና ስላገለገሏቸው ነው’ ብለው ይመልሳሉ።”