ማሕልየ መሓልይ 4

1 ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ!

እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽ

ከመሸፈኛሽ ውስጥ ያሉት ዐይኖችሽ

እንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው፤

ጠጒርሽም ከገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ፣

የፍየል መንጋ ነው።

2 ጥርሶችሽ ወዲያው ተሸልተው፣

ከመታጠቢያ እንደ ወጡ የበግ መንጋ ናቸው፤

ሁሉም መንታ መንታ የወለዱ፣

ከመካከላቸውም መካን የሌለባቸው ናቸው።

3 ከንፈሮችሽ ቀይ የሐር ፈትል ይመስላሉ፤

አፍሽም ውብ ነው፤

ከመሸፈኛሽ ውስጥ ያሉት ጒንጮችሽ፣

ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላሉ።

4 ዐንገትሽ አምሮ የተሠራውን፣

በላዩም የጦረኞች ጋሻዎች ሁሉ ያሉበትን፣

ሺህ ጋሻዎች የተንጠለጠሉበትን፣

የዳዊትን የመጠበቂያ ማማ ይመስላል።

5 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ ሆነው የተወለዱ፣

በውብ አበቦች መካከልም የተሰማሩ፣

ሁለት የሚዳቋ ግልገሎችን ይመስላሉ።

6 ጎሕ ከመቅደዱ በፊት፣

ጥላውም ሳይሸሽ፣

ወደ ከርቤ ተራራ፣

ወደ ዕጣኑም ኰረብታ እወጣለሁ።

7 ውዴ ሆይ፤ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤

እንከንም አይወጣልሽም።

8 ሙሽራዬ ሆይ፤ ከሊባኖስ አብረሽኝ ነዪ፤

አዎን ከሊባኖስ አብረሽኝ ነዪ፤

ከአንበሶች ዋሻ፣

ከነብሮች ተራራ፣

ከኤርሞን ራስ፣ ከሳኔር ጫፍ፣

ከአማና ዐናት ውረጂ።

9 እኅቴ ሙሽራዬ፣ ልቤን ሰርቀሽዋል፤

በአንድ አፍታ እይታሽ፣

ከሐብልሽም በአንዱ ዕንቊ፣

ልቤን ሰርቀሽዋል።

10 እኅቴ ሙሽራዬ፣ ፍቅርሽ እንዴት ደስ ያሰኛል!

ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ ምንኛ

የሚያረካ ነው፤

የሽቱሽም መዐዛ ከቅመም ሁሉ ይልቅ የቱን ያህል ይበልጥ!

11 ሙሽራዬ ሆይ፤ ከንፈሮችሽ የማር ወለላ ያንጠባጥባሉ፤

ከአንደበትሽም ወተትና ማር

ይፈልቃል፤

የልብስሽም መዐዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው።

12 እኅቴ ሙሽራዬ፤ የታጠረ የአትክልት ቦታ፣

ዙሪያውን የተከበበ ምንጭ፣ የታተመም ፏፏቴ ነሽ።

13 ተክልሽ ሮማን፣

ምርጥ ፍሬዎች፣

ሄናና ናርዶስ ያሉበት ነው።

14 እንዲሁም ናርዶስና ቀጋ፣

ጠጅ ሣርና ቀረፋ፣

የተለያዩ የዕጣን ዛፎች፣

ከርቤና እሬት፣

ምርጥ ቅመሞች ሁሉ አሉበት።

15 አንቺየአትክልት ቦታ ፏፏቴ፣

ከሊባኖስ የሚወርድ፣

የፈሳሽ ውሃ ጒድጓድ ነሽ።

16 የሰሜን ነፋስ ሆይ፤ ንቃ፤

የደቡብም ነፋስ ሆይ፤ ና!

መዐዛው ያውድ ዘንድ፣

በአትክልት ቦታዬ ላይ ንፈስ፤

ውዴ ወደ አትክልት ቦታው ይግባ፤

ምርጥ ፍሬዎቹንም ይብላ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *