በጽዮን ጠላቶች ላይ የቀረበ ጸሎት
መዝሙረ መዓርግ
1 እስራኤል እንዲህ ይበል፦
“ከልጅነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ አስጨነቁኝ፤
2 በርግጥ ከልጅነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ አስጨነቁኝ፤
ዳሩ ግን ድል አላደረጉኝም።
3 ዐራሾች ጀርባዬን ዐረሱት፤
ትልማቸውንም አስረዘሙት።”
4 እግዚአብሔርግን ጻድቅ ነው፤
የክፉዎችን ገመድ በጣጥሶ ጣለው።
5 ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ፣
ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።
6 ገና ከመብቀሉ እንደሚደርቅ፣
በጣራ ላይ እንደ በቀለ ሣር ይሁኑ፤
7 ደግሞም ለዐጫጅ እጁን፣
ለነዶ ሰብሳቢ ዕቅፉን እንደማይሞላ ይሁኑ።
8 መንገድ ዐላፊዎችም፣
“የእግዚአብሔርበረከት በእናንተ ላይ ይሁን፤
በእግዚአብሔርስም እንባርካችኋለን” አይበሉ።