የጻድቅ ሰው ባሕርይ
1 ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔርንየሚፈራ፣
በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ የተባረከ ነው።
2 ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤
የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።
3 ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤
ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።
4 ቸር፣ ርኅሩኅና ጻድቅ እንደ መሆኑ፣
ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል።
5 ለጋስና ያለ ማንገራገር የሚያበድር፣
ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል፤
6 ለዘላለም ከስፍራው አይናወጥምና፤
ጻድቅ ሰውሲታወስ ይኖራል።
7 ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤
ልቡእግዚአብሔርንበመተማመን የጸና ነው።
8 ልቡ የጸና ነው፤ አይፈራምም፤
በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል።
9 በልግስና ለድኾች ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፤
ቀንዱምበክብር ከፍ ከፍ ይላል።
10 ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤
ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤
የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች።