ለመለኮቱ ባሕርያት የቀረበ ጸሎት
1 ሃሌ ሉያ።
በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣
ለእግዚአብሔርበፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።
2 የእግዚአሔርሥራ ታላቅ ናት፤
ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል።
3 ሥራው ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው፤
ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
4 ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤
እግዚአብሔርቸር፣ ርኅሩኅም ነው።
5 ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤
ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።
6 ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣
የአሠራሩን ብርታት አሳይቶአል።
7 የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤
ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤
8 ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤
በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።
9 ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤
ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤
ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።
10 እግዚአብሔርንመፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤
ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤
ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።