የእግዚአብሔር ፍትሕ
1 የበቀል አምላክ፣ አንተእግዚአብሔርሆይ፤
የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ።
2 አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤
ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው።
3 ክፉዎች እስከ መቼእግዚአብሔርሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?
4 የእብሪት ቃላት ያዥጐደጒዳሉ፤
ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጒራ ይነዛሉ።
5 እግዚአብሔርሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤
ርስትህንም አስጨነቁ።
6 መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤
የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ።
7 እነርሱም “እግዚአብሔርአያይም፤
የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።
8 እናንት በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤
እናንት ቂሎች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?
9 ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?
10 ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣
ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?
11 እግዚአብሔርየሰው ሐሳብ መና፣
ከንቱም እንደሆነ ያውቃል።
12 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣
ከሕግህም የምታስተምረው ሰው ምስጉን ነው።
13 ለኀጢአተኞች ጒድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣
እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።
14 እግዚአብሔርሕዝቡን አይጥልምና፤
ርስቱንም አይተውም።
15 ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤
ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።
16 ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው?
ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው?
17 እግዚአብሔርረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣
ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር።
18 እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣
እግዚአብሔርሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።
19 የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣
ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
20 ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣
የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር ሊያብር ይችላልን?
21 በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤
በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።
22 ለእኔ ግንእግዚአብሔርምሽግ፣
አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል።
23 በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤
በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤
እግዚአብሔርአምላካችን ይደመስሳቸዋል።