መዝሙር 92

ጻድቅ ሰው ሲደሰት

በሰንበት ቀን የሚዘመር መዝሙር፤ ማሕሌት

1 እግዚአብሔርንማመስገን መልካም ነው፤

ልዑል ሆይ፤ ለስምህ መዘመር ጥሩ ነው፤

2 ምሕረትህን በማለዳ፣

ታማኝነትህንም በሌሊት ማወጅ መልካም ነው፤

3 ዐሥር አውታር ባለው በገና፣

በመሰንቆም ቅኝት ታጅቦ ማወጅ ጥሩ ነው።

4 እግዚአብሔርሆይ፤ በሥራህ ስለ ተደሰትሁ፣

ስለ እጅህ ሥራ በደስታ እዘምራለሁ።

5 እግዚአብሔርሆይ፤ ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው!

ሐሳብህስ ምን ያህል ጥልቅ ነው!

6 ደነዝ ሰው ይህን አያውቅም፤

ነኁላላም አያስተውለውም።

7 ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣

ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣

ለዘላለሙ ይጠፋሉ፤

8 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ።

9 ጠላቶችህእግዚአብሔርሆይ፤ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፤

ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይበተናሉ።

10 የእኔን ቀንድ ግን እንደ አውራሪስ ቀንድከፍ ከፍ አደረግኸው፤

በለጋ ዘይትም አረሰረስኸኝ።

11 ዐይኖቼ የባላንጦቼን ውድቀት አዩ፤

ጆሮዎቼም የክፉ ጠላቶቼን ድቀት ሰሙ።

12 ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤

እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ።

13 በእግዚአብሔርቤት ተተክለዋል፤

በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ።

14 ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤

እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።

15 “እግዚአብሔርትክክለኛ ነው፤

እርሱ ዐለቴ ነው፤ በእርሱ ዘንድ እንከን የለም” ይላሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *