በስደት ጊዜ የቀረበ ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት ትምህርት
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤
ልመናዬን ቸል አትበል፤
2 ወደ እኔ ተመልከት፤ መልስልኝም።
በውስጤ ታውኬአለሁ፤ ተናውጬአለሁም፤
3 በጠላት ድምፅ ተሸበርሁ፤
በክፉዎች ድንፋታ ደነገጥሁ፤
መከራ አምጥተውብኛልና፤
በቍጣም ተነሣሥተው ጠላት ሆነውብኛል።
4 ልቤ በውስጤ ተጨነቀብኝ፤
የሞት ድንጋጤም በላዬ መጣ።
5 ፍርሀትና እንቅጥቃጤ መጣብኝ፤
ሽብርም ዋጠኝ።
6 እኔም እንዲህ አልሁ፤ “ምነው የርግብ ክንፍ በኖረኝ!
በርሬ በሄድሁና ባረፍሁ ነበር፤
7 እነሆ፤ ኰብልዬ በራቅሁ፣
በምድረ በዳም በሰነበትሁ ነበር፤ሴላ
8 ከዐውሎ ነፋስና ከውሽንፍር ሸሽቼ፣
ወደ መጠለያዬ ፈጥኜ በደረስሁ ነበር።”
9 ጌታ ሆይ፤ ግፍንና ሁከትን በከተማዪቱ ውስጥ አይቼአለሁና፣
ግራ አጋባቸው፤ ቋንቋቸውንም ደበላልቅ።
10 ቀንና ሌሊት ቅጥሯ ላይ ወጥተው ይዞሯታል፤
ተንኰልና መከራ በውስጧ አለ።
11 ጥፋት በመካከሏ ይገኛል፤
ግፍና አታላይነትም ከጎዳናዋ አይጠፋም።
12 የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤
ቢሆንማ ኖሮ በታገሥሁት ነበር፤
የሚጠላኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤
ቢሆንማ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።
13 ነገር ግን አድራጊው አንተ ነህ፤ እኩያዬ፣ ባልንጀራዬና ወዳጄ፤
14 በእግዚአብሔርም ቤት አብረን በሕዝብ መካከል ተመላለስን፤
ደስ የሚል ፍቅር በአንድነት ነበረን።
15 ሞት ሳይታሰብ ድንገት ይምጣባቸው፤
በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦልይውረዱ፤
ክፋት በመካከላቸው አድራለችና።
16 እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤
እግዚአብሔርምያድነኛል።
17 በማታ፣ በጥዋትና በቀትር፣
እጮኻለሁ፤ እቃትታለሁም፤
እርሱም ድምፄን ይሰማል።
18 በተቃውሞ የተነሡብኝ ብዙዎች ናቸውና፣
ከተቃጣብኝ ጦርነት፣
ነፍሴን በሰላም ይቤዣታል።
19 አካሄዳቸውን አልቀየሩምና፣
እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና፣
ከጥንት ጀምሮ በዙፋኑ ላይ ያለ አምላክ፣ሴላ
ሰምቶ ያዋርዳቸዋል።
20 ባልንጀራዬ የምለው ሰው እጁን
በወዳጆቹ ላይ ሰነዘረ፤
ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ።
21 አፉ ከቅቤ ይልቅ የለዘበ ነው፤
በልቡ ግን ጦርነት አለ፤
ቃሉ ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነው፤
ይሁን እንጂ የተመዘዘ ሰይፍ ነው።
22 የከበደህን ነገርበእግዚአብሔርላይ ጣል፤
እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤
የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።
23 አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎችን ወደ ጥፋት ጒድጓድ
ታወርዳቸዋለህ፤
ደም የተጠሙ ሰዎችና አታላዮች፣
የዘመናቸውን እኩሌታ አይኖሩም።
እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ።