አምላክ የለሾች
ለመዘምራን አለቃ፤ በማኸላት፤ የዳዊት ትምህርት።
1 ቂል በልቡ፣
“እግዚአብሔር የለም” ይላል።
ብልሹዎች ናቸው፤ ተግባራቸውም ጸያፍ ነው፤
በጎ ነገርን የሚያደርግ አንድ እንኳ የለም።
2 በማስተዋል የሚመላለስ፣
እግዚአብሔርን የሚፈልግ እንዳለ ለማየት፣
እግዚአብሔር ከሰማይ፣
ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ።
3 ሁሉም ወደ ሌላ ዘወር አሉ፤
በአንድነትም ተበላሹ፤
አንድ እንኳ፣
በጎ የሚያደርግ የለም።
4 ሰው እንጀራ እንደሚበላ ሕዝቤን የሚበሉት፣
እግዚአብሔርንም ጠርተው የማያውቁት፣
እነዚያ ክፉ አድራጊዎች ከቶ አይማሩምን?
5 የሚያስፈራ ነገር በሌለበት፣
በዚያ፣ በፍርሀት ተዋጡ፤
እግዚአብሔር የዘመቱብህን ሰዎች ዐጥንት በተነ፤
እርሱ እግዚአብሔር ስለ ናቃቸው፣ አንተ አሳፈርሃቸው።
6 ምነው ለእስራኤል የሚሆን መዳን ከጽዮን በወጣ!
እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፣
ያዕቆብ ሐሤት ያድርግ፤ እስራኤል ደስ ይበለው።