የክፉዎች ዕጣ ፈንታ
ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቶአል” ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት
ትምህርት
1 ኀያል ሆይ፤ በክፋት ለምን ትኵራራለህ?
አንተ በእግዚአብሔር ዐይን የተናቅህ፣
እንዴትስ ዘወትር ትታበያለህ?
2 አንተ ማታለልን ሥራዬ ብለህ የያዝህ፤
አንደበትህ እንደ ሰላ ምላጭ፣
ጥፋትን ያውጠነጥናል።
3 ከበጎ ነገር ይልቅ ክፋትን፣
እውነትን ከመናገር ይልቅ ሐሰትን ወደድህ።ሴላ
4 አንተ አታላይ አንደበት ሆይ፤
ጐጂ ቃላትን ሁሉ ወደድህ!
5 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም
ያንኰታኵትሃል፤
ይነጥቅሃል፤ ከድንኳንህም መንጥቆ ያወጣሃል፤
ከሕያዋንም ምድር ይነቅልሃል።ሴላ
6 ጻድቃን ይህን ዐይተው ይፈራሉ፤
እንዲህ እያሉም ይሥቁበታል፤
7 “እግዚአብሔርን መጠጊያ ያላደረገ፣
ነገር ግን በሀብቱ ብዛት የተመካ፣
በክፋቱም የበረታ፣
ያ ሰው እነሆ!”
8 እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት፣
እንደለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤
ከዘላለም እስከ ዘላለም፣
በእግዚአብሔር ምሕረት እታመናለሁ።
9 ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤
ስምህ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ፤
በቅዱሳንም መካከል አመሰግንሃለሁ።