መዝሙር 40

የምስጋናና የርዳታ ልመና ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔርንደጅ ጠናሁት፤

እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ።

2 ከሚውጥ ጒድጓድ፣

ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤

እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤

አካሄዴንም አጸና።

3 ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣

አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤

ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤

በእግዚአብሔርይታመናሉ።

4 እግዚአብሔርንመታመኛው ያደረገ፣

ወደ ትዕቢተኞች የማይመለከት፣

የሐሰት አማልክትንወደሚከተሉት የማያይ፣

ሰው ብፁዕ ነው።

5 እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤

አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤

ለእኛ ያቀድኸውን፣

ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤

ላውራው ልናገረው ብል፣

ስፍር ቍጥር አይኖረውም።

6 መሥዋዕትንና ቊርባንን አልፈለግህም፤

ጆሮቼን ግን ከፈትህ፤

የሚቃጠል መሥዋዕትን፣

የኀጢአትንም መሥዋዕት አልሻህም።

7 እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤

ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤

8 አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤

ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።”

9 በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤

እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣

ከንፈሮቼን አልገጠምሁም።

10 ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤

ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤

ምሕረትህንና እውነትህን፣

ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም።

11 እግዚአብሔርሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤

ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤

12 ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከቦኛልና፤

የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤

ከራሴ ጠጒር ይልቅ በዝቶአል፤

ልቤም ከድቶኛል።

13 እግዚአብሔርሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤

እግዚአብሔርሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

14 ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ፣

ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤

ጒዳቴንም የሚሹ፣

ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ።

15 በእኔ ላይ፣ “እሰይ! እሰይ!” የሚሉ፣

በራሳቸው እፍረት ይደንግጡ።

16 አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣

ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤

ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወዱ፣

“እግዚአብሔርከፍ ከፍ ይበል” ይበሉ።

17 እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝ፤

ጌታ ግን ያስብልኛል።

አንተ ረዳቴና አዳኜ ነህ፤

አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *