እግዚአብሔር የጽድቅ ፀሓይ
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር
1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤
የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።
2 ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤
ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤
3 ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤
ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም።
4 ያም ሆኖ ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣
ቃላቸውምእስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል።
እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሎአል፤
5 ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤
ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል።
6 መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤
ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤
ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።
7 የእግዚአብሔርሕግ ፍጹም ነው፤
ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤
የእግዚአብሔርሥርዐት የታመነ ነው፤
አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
8 የእግዚአብሔርሕግጋት ትክክል ናቸው፤
ልብን ደስ ያሰኛሉ።
የእግዚአብሔርትእዛዝ ብሩህ ነው፤
ዐይንን ያበራል።
9 እግዚአብሔርንመፍራት ንጹሕ ነው፤
ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
የእግዚአብሔርፍርድ የታመነ፣
ሁለንተናውም ጻድቅ ነው፤
10 ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣
እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤
ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤
ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል።
11 ደግሞም አገልጋይህ በእርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤
እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።
12 ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል?
ከተሰወረ በደል አንጻኝ።
13 ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤
እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤
ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤
ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።
14 መጠጊያዬና አዳኜእግዚአብሔርሆይ፤
የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣
በፊትህ ያማረ ይሁን።