በአምላኩ የታመነ ሰው አቤቱታ
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔርሆይ፤ እስከ መቼ ድረስ ለዘላለሙ ትረሳኛለህ?
ፊትህንስ ከእኔ የምትሰውረው እስከ መቼ ድረስ ነው?
2 ከሐሳቤ ጋር የምሟገተው፣
ልቤም ቀኑን ሙሉ የሚያዝነው እስከ መቼ ነው?
ጠላቴስ በእኔ ላይ የሚያይለው እስከ መቼ ድረስ ነው?
3 እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤ ተመልከት፤
ስማኝም፤
የሞት እንቅልፍ እንዳልተኛ ዐይኖቼን አብራ፤
4 በዚህም ጠላቴ፣ “አሸነፍሁት” እንዳይል፣
ባላጋራዎቼም በውድቀቴ ደስ እንዳይላቸው ርዳኝ።
5 እኔ ግን በጸናች ፍቅርህ እታመናለሁ፤
ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል።
6 ቸርነቱ በዝቶልኛልና፣
ለእግዚአብሔርእዘምራለሁ።