መዝሙር 8

የፈጣሪ ግርማ በፍጥረቱ ላይ

ለመዘምራን አለቃ፣ በዋሽንት የሚዜም፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔርአምላካችን ሆይ፤

ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!

ክብርህ ከሰማያት በላይ፣

ከፍ ከፍ ብሎአል።

2 ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ ሕፃናት አፍ፣

ምስጋናንአዘጋጀህ፤

ከጠላትህ የተነሣ፣

ባላንጣንና ቂመኛን ጸጥ ታሰኝ ዘንድ።

3 የጣቶችህን ሥራ፣

ሰማያትህን ስመለከት፣

በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣

ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣

4 በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?

ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?

5 ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤

የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው።

6 በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት፤

7 በጎችንና ላሞችን ሁሉ፣

የዱር አራዊትንም፣

8 የሰማይ ወፎችንና፣

የባሕር ዓሦችን፣

በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትንም ሁሉ አስገዛህለት።

9 እግዚአብሔርአምላካችን ሆይ፤

ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *