1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በደኅና በተመለሰ ጊዜ፣
2 ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፣ “አንተ ክፉውን መርዳትህናእግዚአብሔርንየሚጠሉትን ማፍቀርህተገቢ ነውን? ስለዚህየእግዚአብሔርቊጣ ባንተ ላይ ነው፤
3 ይሁን እንጂ የአሼራን ዐምዶች ከምድሪቱ ስላስወገድህና እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልብህን ስላዘጋጀህ፣ መልካም ነገር ተገኝቶብሃል”።
ኢዮሣፍጥ ዳኞችን ሾመ
4 ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ከቤርሳቤህ እስከ ኰረብታማው አገር እስከ ኤፍሬም ድረስ እንደ ገና በመውጣት ወደ ሕዝቡ መካከል ገብቶ ወደ አባቶቻቸውአምላክወደ እግዚአብሔር መለሳቸው።
5 በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ዳኞችን ሾመ፤
6 እንዲህም አላቸው፤ “እናንተ የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን፣ ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ ጋር ለሆነውለእግዚአብሔርስለ ሆነ፣ በምትሰጡት ውሳኔ ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤
7 አሁንምእግዚአብሔርንመፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤በአምላካችንበእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ማጣመም፣ አድልዎ ማድረግና መማለጃ መቀበል ስለሌለ ተጠንቅቃችሁ ፍረዱ።”
8 ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌምየእግዚአብሔርንሕግ እንዲያስፈጽሙና ለሚነሡ ክርክሮችም እልባት እንዲሰጡ ከሌዋውያን፣ ከካህናትና ከእስራኤል ቤትአለቆች ጥቂት ሰዎች ሾመ፤ እነርሱም መኖሪያቸው በኢየሩሳሌም ሆነ።
9 እነርሱንም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “እግዚአብሔርንበመፍራት፣ በታማኝነትና በፍጹም ልብ አገልግሉ።
10 በየከተማው ከሚኖሩት ወገኖቻችሁ ስለ ደም መፋሰስ ወይም ሕግን፣ ትእዛዛትን፣ ደንብንና ሥርዐትን ስለ መተላለፍ በሚቀርብላችሁ በማናቸውም ጒዳይእግዚአብሔርንእንዳይበድሉ አስጠንቅቋቸው፤ ያለዚያ ግን ቊጣው በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ ይመጣል፤ ይህን ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።
11 “የእግዚአብሔርበሆነው ነገር ሁሉ ላይ የካህናቱ አለቃ አማርያ፣ የንጉሡ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የይሁዳ ነገድ መሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑ ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ሆነው ያገለግላሉ፤ በርትታችሁ ሥሩ፤እግዚአብሔርምመልካም ከሚያደርጉ ጋር ይሁን።”