2 ዜና መዋዕል 6

1 ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔርጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሮአል፤

2 እኔም አንተ ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ፣ ይህን ታላቅና ድንቅ ቤተ መቅደስ ሠራሁልህ።”

3 መላው የእስራኤል ጉባኤ እዚያው ቆመው ሳሉ፣ ንጉሡ ዘወር ብሎ ባረካቸው፤

4 እንዲህም አለ፤

“ለአባቴ ለዳዊት በቃሉ የሰጠውን ተስፋ በእጁ የፈጸመ የእስራኤልአምላክእግዚአብሔር ይመስገን፤ እንዲህ ብሏልና፤

5 ‘ሕዝቤን ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ይሠራበት ዘንድ ከማናቸውም የእስራኤል ነገድ ከተሞች አንድም አልመረጥሁም፤ ወይም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም።

6 አሁን ግን ስሜ በዚያ እንዲሆን ኢየሩሳሌምን፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲገዛም ዳዊትን መርጫለሁ።”

7 “አባቴ ዳዊት፣ ለእስራኤል አምላክለእግዚአብሔርስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤

8 እግዚአብሔርግን፣ ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ አለው፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ አስበህ ነበር፤ ይህን በልብህ በማሰብህ መልካም አድርገሃል፤

9 ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’

10 “እግዚአብሔርምየተናገረውን ቃል ፈጽሞአል፤ እኔምእግዚአብሔርበሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክለእግዚአብሔርምስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ።

11 በዚያምእግዚአብሔርከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”

ሰሎሞን በምረቃው ጊዜ ያቀረበው ጸሎት

12 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባሉበትበእግዚአብሔርመሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ።

13 ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድየሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፣

14 እንዲህም አለ፤

“የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋር የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤

15 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።

16 “አሁንም የእስራኤልአምላክእግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ከቶ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት።

17 እንግዲህ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

18 “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!

19 ይሁን እንጂ እግዚአብሔርአምላኬሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ።

20 ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዓይኖችህ በቀንም በሌሊትም የተገለጡ ይሁኑ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ።

21 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸል ዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

22 አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣

23 ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው።

24 “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣

25 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።

26 “ሕዝብህ አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ባይዘንብ፣ አንተ ስለአስጨነቅሃቸው ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፣ ስምህን ቢጠሩና ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣

27 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚኖሩበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ በሰጠኸውም ምድር ላይ ዝናብን ላክ።

28 “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ በሚወርድባት ጊዜ፣ ወይም ደግሞ በየትኛውም ከተማቸው ሳሉ ጠላት በሚከባቸው ጊዜ፣ ወይም ማናቸውም አደጋ ወይም ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፣

29 ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንም ሰው ጭንቀቱና ሕመሙ ተሰምቶት፣ እጁን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ፣

30 በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ ይቅርም በል፤ የሰውን ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ክፈለው፤

31 ይህም ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህና በመንገዶችህ እንዲሄዱ ነው።

32 “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ ባዕድ ሰው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ኀያሉ እጅህና ስለ ተዘረጋው ክንድህ ሰምቶ ከሩቅ አገር በመምጣት ወደዚህ ቤተ መቅደስ በሚጸልይበት ጊዜ፣

33 በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።

34 “ሕዝብህ አንተ በምትልካቸው ቦታ ሁሉ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣

35 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ የጠየቁህንም አድርግላቸው።

36 “መቼም የማይበድል ሰው የለምና፣ አንተን በበደሉህ ጊዜ፣ ተቈጥተሃቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር በምርኮ ለሚወስዳቸው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣

37 በተማረኩበት አገር ሆነው የልብ ጸጸት ተሰምቶአቸው ንስሐ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ቢሉ፣

38 ተማርከው በሚኖሩበትም ምድር ሆነው በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥኻት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣

39 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ በማደሪያህ ስማ፤ የጠየቊህንም አድርግላቸው። የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል።

40 አሁንም አምላኬ ሆይ፤ በዚህ ስፍራ ወደ ቀረበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፣ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ።

41 “አሁንም እግዚአብሔርአምላክሆይ ተነሥ፣ ከኀይልህ ታቦት ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ።

እግዚአብሔርአምላክ ሆይ፤ ካህናትህ ድነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በቸርነትህ ደስ ይበላቸው።

42 እግዚአብሔርአምላክ ሆይ፤ የቀባኸውን አትተወው፤ ለባሪያህ ለዳዊት ቃል የገባህለትን ጽኑ ፍቅር አስብ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *