1 ከዚያም ዳዊት፣ “ከእንግዲህየእግዚአብሔርአምላክ ቤት በዚህ ይሆናል፤ እንዲሁም ስለ እስራኤል የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚሁ ይቆማል” አለ።
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
2 ስለዚህ ዳዊት በእስራኤል የሚኖሩ መጻተኞች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ከመካከላቸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ጥርብ ድንጋይ እንዲያዘጋጁ ጠራቢዎችን መደበ።
3 ለቅጥር በሮቹ ምስማርና ማጠፊያ የሚሆን ብዙ ብረትና ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስ አዘጋጀ።
4 እንዲሁም ሲዶናውያንና ጢሮሳውያን በብዛት አምጥተውለት ስለ ነበር፣ ስፍር ቍጥር የሌለው የዝግባ ዕንጨት አሰናዳ።
5 ዳዊትም፣ “ልጄ ሰሎሞን ወጣት ነው፤ ልምዱም የለውም፤ለእግዚአብሔርየሚሠራው ቤተ መቅደስ ደግሞ እጅግ የሚያምር፣ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ ዝናው የተሰማና እጅግ የተዋበ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ሁሉንም እኔ አዘጋጃለሁ” አለ። እንዳለውም ዳዊት ከመሞቱ በፊት በብዛት አዘጋጀ።
6 ከዚያም ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክለእግዚአብሔርቤት እንዲሠራ አዘዘው።
7 ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፤ ለአምላኬለእግዚአብሔርስም ቤት ለመሥራት በልቤ አስብ ነበር፤
8 ነገር ግንከእግዚአብሔርእንዲህ የሚል ቃል መጣልኝ፤ “አንተ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ብዙ ጦርነትም አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም ያፈሰስህ ስለ ሆነ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራልኝም፤
9 ነገር ግን የሰላምና የዕረፍት ሰው የሆነ ልጅ ትወልዳለህ፤ በየአቅጣጫው ካሉ ጠላቶቹ ዐሳርፈዋለሁ፤ ስሙም ሰሎሞን ይባላል። በዘመኑም ለእስራኤል ሰላምንና ጸጥታን እሰጣለሁ።
10 ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ እርሱ ነው። እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። ዙፋኑንም በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።
11 “አሁንም ልጄ ሆይ፤እግዚአብሔርከአንተ ጋር ይሁን፤ እንድትፈጽመው በተናገረውም መሠረት፣ ተሳክቶልህ የአምላክህንየእግዚአብሔርንቤት ለመሥራት ያብቃህ።
12 በእስራኤል ላይ አለቃ ባደረገህ ጊዜ፣ የአምላክህንየእግዚአብሔርንትእዛዝ ትፈጽም ዘንድእግዚአብሔርጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ።
13 እግዚአብሔርበሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጉንና ሥርዐቱን ተጠንቅቀህ ብትጠብቅ ይሳካልሃል፤ አይዞህ ጠንክር፤ በርታ፤ ተስፋም አትቊረጥ።
14 “ለእግዚአብሔርቤት እንዲሆንም አንድ ሺህ መክሊትወርቅ፣ አንድ ሚሊዮን መክሊትብር፣ ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ለማዘጋጀት በተቻለኝ ሁሉ ጥሬአለሁ። በተረፈ አንተ ጨምርበት።
15 ድንጋይ ጠራቢዎች፣ ግንበኞች፣ አናጢዎች የሆኑ ብዙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ የተጠበቡ ሰዎች አሉህ፤
16 እነዚህም ቊጥራቸው እጅግ የበዛ የወርቅ፣ የብር፣ የናስና የብረት ሠራተኞች ናቸው። በል ሥራህን ጀምር፤እግዚአብሔርምከአንተ ጋር ይሁን።”
17 ከዚያም ዳዊት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ልጁን ሰሎሞንን እንዲረዱት አዘዘ፤
18 እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔርአምላካችሁ እስካሁን ከእናንተ ጋር አይደለምን? በየአቅጣጫውስ ዕረፍትን ሰጥቷችሁ የለምን? የምድሪቱን ነዋሪዎች በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኛል፤ ምድሪቱምለእግዚአብሔርናለሕዝቡ ተገዝታለች።
19 አሁንምእግዚአብሔርአምላካችሁን ለመፈለግ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ሰብስቡ።የእግዚአብሔርንየኪዳኑን ታቦትና ንዋያተ ቅድሳቱን ለእግዚአብሔር ስም ወደሚሠራው ቤተ መቅደስ አምጥታችሁ የአምላክንየእግዚአብሔርንመቅደስ ሥሩ።”