ኤልያስ ወደ ኮሬብ ኰበለለ
1 አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት።
2 ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
3 ኤልያስም ፈርቶስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤
4 በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔርሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ።
5 ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው።
በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።
6 ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ እንጎቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።
7 የእግዚአብሔርምመልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው።
8 ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደእግዚአብሔርተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤
9 በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ።
እግዚአብሔር ለኤልያስ ተገለጠለት
የእግዚአብሔርምቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።
10 እርሱም፣ “እኔ ለሰራዊት ጌታለእግዚአብሔርእጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።
11 እግዚአብሔርም፣“እግዚአብሔርበዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህበእግዚአብሔርፊት ቁም” አለው።
ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንምበእግዚአብሔርፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤እግዚአብሔርግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤እግዚአብሔርግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም።
12 ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤እግዚአብሔርግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስ ለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።
13 ኤልያስም ይህን ሲሰማ፣ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፍኖ ወጣና በዋሻው ደጃፍ ቆመ።
ከዚያም፣ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።
14 እርሱም፣ “እኔ ሁሉን ለሚችል ጌታለእግዚአብሔርእጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።
15 እግዚአብሔርምእንዲህ አለው፤ “በመጣህበት መንገድ ተመልሰህ ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ሂድ፤ እዚያ ስትደርስም አዛሄልን በሶርያ ላይ እንዲነግሥ ቅባው።
16 እንዲሁም የናሜሲን ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ቅባው፤ ደግሞም ነቢይ ሆኖ በእግርህ እንዲተካ የአቤል ምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው።
17 ከአዛሄል ሰይፍ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።
18 እኔም ጒልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺህ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ።”
የኤልሳዕ መጠራት
19 ስለዚህ ኤልያስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬ አውጥቶ ራሱ በዐሥራ ሁለተኛው ጥማድ በሬ ሲያርስ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ መጥቶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት።
20 ከዚያም ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ፣ “አባቴንና እናቴን ስሜ እንድሰናበታቸው ፍቀድልኝ፤ ከዚያም እከተልሃለሁ” አለው።
ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ ምን ያደረግሁህ ነገር አለ? ልትመለስ ትችላለህ” አለው።
21 ስለዚህም ኤልሳዕ ትቶት ተመለሰ። ሁለቱን በሬዎቹን ወስዶ ዐረደ፤ የዕርሻ ዕቃውን አንድዶ ሥጋቸውን በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነርሱም በሉ። ከዚያም ኤልያስን ለመከተል ሄደ፤ ረዳቱም ሆነ።