1 ነገሥት 14

አኪያ በኢዮርብዓም ላይ የተናገረው ትንቢት

1 በዚያን ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ፤

2 ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፤ “ተነሺ፣ የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽ እንዳይታወቅብሽ ሆነሽ፣ ወደ ሴሎ ሂጂ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢይ አኪያ እነሆ፤ በዚያ ይገኛል።

3 ስትሄጂም ዐሥር እንጀራ፣ ጥቂት ሙልሙል ዳቦ እና አንድ እንስራ ማር ይዘሽ ሂጂ፤ እርሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ይነግርሻል።”

4 ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ያላትን አድርጋ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች።

በዚህ ጊዜ አኪያ ከማርጀቱ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዘው ነበር።

5 እግዚአብሔርግን ለአኪያ፣ “እነሆ፤ የኢዮርብዓም ሚስት ስለ ታመመው ልጇ ልትጠይቅህ ሌላ ሴት መስላ ትመጣለችና እንዲህ ብለህ መልሳት” ብሎ ነገረው።

6 አኪያም የእግሯን ኮቴ ድምፅ እበሩ ላይ እንደ ሰማ እንዲህ አላት፤ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ ግቢ፤ ግን ለምንድን ነው ሌላ ሴት መስለሽ ለመታየት የፈለግሽው? ለአንቺ ከባድ ነገር እንድነግርሽ ተልኬአለሁ።

7 አሁንም ሂጂና ኢዮርብዓምን የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርየሚለው ይህ ነው ብለሽ ንገሪው፤ ‘ከሕዝቡ መካከል አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤

8 ከዳዊት ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ አንተ ግን በፊቴ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ትእዛዜን እንደ ጠበቀው፣ በፍጹም ልቡም እንደ ተከተለኝ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም።

9 ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቊጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።

10 “ ‘ስለዚህ እኔም በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ የኢዮርብዓምን ወንድ ልጅ ሁሉ ከእስራኤል አስወግዳለሁ፤ ኩበትም ዐመድ እስኪሆን ድረስ እንደሚቃጠል፣ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት እንዲሁ አቃጥላለሁ።

11 ከኢዮርብዓም ወገን በከተማ የሞተውን ውሾች፣ በባላገር የሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤እግዚአብሔርተናግሮአልና!’

12 “እንግዲህ አንቺም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የምትኖሪበትን ከተማ እግርሽ እንደ ረገጠ፣ ልጁ ይሞታል፤

13 እስራኤልም ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል። የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ በወግ በማዕረግ የሚቀበር እርሱ ብቻ ነው።

14 “ከዚህም በላይ፣እግዚአብሔርየኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ የሚያስወግድ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ለራሱ ያስነሣል፤ ይህም ዛሬ፣ አሁኑኑ ይሆናል።

15 እግዚአብሔርእስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድበመሥራትእግዚአብሔርንለቊጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣እግዚአብሔርለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶይበትናቸዋል።

16 ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣እግዚአብሔርእስራኤልን ይተዋቸዋል።

17 የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤

18 ከዚያም ቀበሩት፤እግዚአብሔርበባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።

19 የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

20 እርሱም ሃያ ሁለት ዓመት ነግሦ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ናዳብም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም

21 የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱምእግዚአብሔርለስሙ መጠሪያ እንድትሆን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱ ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።

22 ይሁዳበእግዚአብሔርፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቊጣውን አነሣሡ፤

23 እንዲሁም በእያንዳንዱ ኰረብታና በየትልልቁ ዛፍ ጥላ ሥር የማምለኪያ ኰረብቶችን አዕማደ ጣዖታት፣ የአሼራን ምስል ዐምድ ለራሳቸው አቆሙ።

24 ከዚያም ይልቅ፣ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩ፤እግዚአብሔርከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ የፈጸሙትን አስጸያፊ ድርጊት ሁሉ እነዚህም ፈጸሙ።

25 ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ፤

26 የእግዚአብሔርንቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች እንኳን ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር አጋዘ።

27 ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን በር የሚጠብቁት ዘበኞች አዛዦች እንዲይዙ አደረገ።

28 ንጉሡ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን ያነግባሉ፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር።

29 የቀረው የሮብዓም አገዛዝ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

30 በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ያላቋረጠ ጦርነት ተደርጎ ነበር።

31 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። እናቱ ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። ልጁ አብያምበእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *