ንግሥተ ሳባ ሰሎሞንን እንደ ጐበኘች
1 ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ዝና እናከእግዚአብሔርስም ጋር ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች።
2 ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቶ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ዕንቆች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት።
3 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ንጉሡ አቅቶት የቀረ አንዳች ጥያቄ አልነበረም።
4 ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት
5 እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አሳላፊዎቹን ከነደንብ ልብሳቸው፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ ደግሞምበእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ያቀረበውን የሚቃጠል መሥዋዕትስታይ እጅግ ተደነቀች።
6 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስላከናወንኸው ሥራና ስለ ጥበብህ ባገሬ ሳለሁ የሰማሁት ትክክል ነው፤
7 ይሁን እንጂ፣ ራሴ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በእርግጥ ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት በላይ ነው።
8 ሰዎችህ እንዴት ያሉ ዕድለኞች ናቸው! ሁል ጊዜ በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ እንዴት የታደሉ ናቸው!
9 በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህእግዚአብሔርአምላክህ የተመሰገነ ይሁን፤እግዚአብሔርበዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።”
10 ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊትወርቅ፣ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ድንጋይ ሰጠችው፤ ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ሽቶ ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።
11 ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትናየከበሩ ዕንቆችም አመጡ።
12 ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨትለእግዚአብሔርቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ መደገፊያ፣ ለበገናና ለመሰንቆ መሥሪያ አዋለው። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዕንጨት እስከ ዛሬ ድረስ ከቶ አልመጣም፤ አልታየምም።
13 ንጉሥ ሰሎሞንም ለንግሥተ ሳባ ከቤተ መንግሥቱ በልግስና ከሚሰጣት ሌላ፣ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።
የሰሎሞን ብልጽግናና ክብር
14 ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበር።
15 ይህም ከንግድና ከሌላ ገቢ ላይ የሚከፈለውን ቀረጥ፣ የዐረብ ነገሥታት ሁሉ የሚያገቡትንና አገረ ገዦች የሚሰበስቡትን ግብር ሳይጨምር ነው።
16 ንጉሥ ሰሎሞን ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ሦስት መቶ ሰቅልወርቅ ነበር።
17 እንዲሁም ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ደግሞ ሦስት ምናንወርቅ ነው። ንጉሡም እነዚህን የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት አኖረ።
18 ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው።
19 ዙፋኑ ባለ ስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል።
20 በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም።
21 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም።
22 ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦችነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።
23 ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።
24 ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።
25 በየዓመቱም የሚመጣውን ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ሽቶ፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።
26 ሰሎሞን ሠረገሎችናፈረሶች ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት። እነዚህንም ሁሉ ሠረገሎች በሚያኖርበት ከተሞችና ራሱ በሚኖርበት በኢየሩሳሌም እንዲሆኑ አደረገ።
27 ንጉሡም ብሩን በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገ፤ የዝግባውም ዕንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።
28 የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብፅናከቀዌሲሆን፣ እነዚህንም ከቀዌ ገዝተው ያመጧቸው የቤተ መንግሥቱ ንግድ ሰዎች ነበሩ።
29 አንዱን ሠረገላ ከግብፅ የሚያመጡት በስድስት መቶ ሰቅልብር ሲሆን፣ ፈረሱን ደግሞ በመቶ አምሳ ሰቅልብር ያመጡ ነበር፤ ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታትም አምጥተው ይሸጡላቸው ነበር።