መሳፍንት 10

ቶላ

1 ከአቤሜሌክ በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ፣ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ሳምር በምትባል መንደር ይኖር ነበር።

2 ቶላ በእስራኤል ላይ ሃያ ሦስት ዓመት በፈራጅነት ከተቀመጠ በኋላ ሞተ፤ በሳምርም ተቀበረ።

ኢያዕር

3 ከቶላ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ ሃያ ሁለት ዓመት በፈራጅነትተቀመጠ።

4 ኢያዕር በሠላሳ አህዮች የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ልጆቹም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች ተብለው የሚጠሩ ሠላሳ ከተሞች በገለዓድ ምድር ነበሯቸው።

5 ኢያዕር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።

ዮፍታሔ

6 እስራኤላውያን እንደ ገናበእግዚአብሔርላይ ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ በኣልንና አስታሮትን እንዲሁም የሶሪያን፣ የሲዶናን፣ የሞዓብን፣ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፤ እስራኤላውያንእግዚአብሔርንስለተዉና ስላላገለገሉት፣

7 ተቈጣቸው፤ በፍልስጥኤማውያንና በአሞናውያን እጅ ሸጣቸው፤

8 እነርሱም በዚያን ዓመት ሰበሯቸው፤ አደቀቋቸውም፤ እስራኤላውያንን ሁሉ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በገለዓድ ምድር፣

9 በአሞራውያን አገር ዐሥራ ስምንት ዓመት እንዲሁም አሞናውያን ይሁዳን፣ ብንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ስለ ተሻገሩ እስራኤላውያን እጅግ ተጨነቁ።

10 ከዚያም እስራኤላውያን አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደእግዚአብሔርጮኹ።

11 እግዚአብሔርምመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብፃውያን፣ አሞራውያን፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣

12 ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ማዖናውያንአሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን?

13 እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤

14 ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስቲ ያድኗችሁ።”

15 እስራኤላውያንምእግዚአብሔርን፣“ኀጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት።

16 ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤እግዚአብሔርንምአመለኩ፤እግዚአብሔርምእስራኤል ስትጐሳቈል ዝም ብሎ ማየት አልቻለም።

17 አሞናውያን ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በገለዓድ በሰፈሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።

18 የገለዓድ ሕዝብ አለቆችም እርስ በእርሳቸው፣ “በአሞናውያን ላይ ጦርነቱን የሚጀምር ሰው በገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል” ተባባሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *