ኢያሱ ለመሪዎች የተናገረው የመሰናበቻ ቃል
1 እግዚአብሔርእስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን አለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር፤
2 ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቶአል።
3 አምላካችሁእግዚአብሔርስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማናቸውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁእግዚአብሔርነው።
4 ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕርድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።
5 ራሱ አምላካችሁእግዚአብሔርከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁእግዚአብሔርበሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።
6 “በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ።
7 በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር አትተባበሩ፤ የአማልክቶቻቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤
8 ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁንእግዚአብሔርንአጥብቃችሁ ያዙ።
9 “እግዚአብሔርታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።
10 አምላካችሁእግዚአብሔርበሰጣችሁ ተስፋ መሠረት የሚዋጋላችሁ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ አንዱ ሰው ሺውን ያሳድዳል።
11 ስለዚህ አምላካችሁንእግዚአብሔርንለመውደድ ተጠንቀቁ።
12 ነገር ግን ከእርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣
13 አምላካችሁእግዚአብሔርከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁእግዚአብሔርከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል።
14 “እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁእግዚአብሔርከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።
15 ነገር ግን አምላካችሁእግዚአብሔርየሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁእግዚአብሔርከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል።
16 አምላካችሁእግዚአብሔርያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸውየእግዚአብሔርቊጣ በላያችሁ ይነዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”