ኢያሱ 20

የመማጠኛ ከተሞች

1 ከዚያምእግዚአብሔርኢያሱን እንዲህ አለው፤

2 “በሙሴ በኩል በነገርኋችሁ መሠረት የመማጠኛ ከተሞች እንዲለዩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤

3 ሳያስበው ድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ወደዚያ በመሸሽ ከደም ተበቃዩ እንዲያመልጥ ከተማዪቱ መጠለያ ትሁን።

4 “ገዳዩ ከነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በሚሸሽበት ጊዜ፣ በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ቆሞ ጒዳዩን ለከተማዪቱ ሽማግሌዎች ይንገራቸው፤ ከዚያም እነርሱ ወደ ከተማቸው አስገብተው የሚኖርበትን ስፍራ ሰጥተውት አብሮአቸው ይቀመጥ።

5 ደም ተበቃዩ ተከታትሎት ቢመጣ፣ ሆን ብሎና በክፋት ተነሣሥቶ ወንድሙን የገደለው ባለመሆኑ፣ ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት።

6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብና በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቆይ። ከዚያም ወደ ቤቱ፣ ሸሽቶ ወደ መጣበት ከተማ ሊመለስ ይችላል።”

7 ስለዚህም በኰረብታማው በንፍታሌም ምድር በገሊላ ቃዴስን፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ሴኬምን፣ በኰረብታማው በይሁዳ ምድር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያት አርባቅን ለዩ።

8 እንደዚሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ከኢያሪኮበስተምስራቅ በሮቤል ነገድ ይዞታ ውስጥ ከፍታ ባለው ምድረ በዳ ያለችውን ቦሶርን፣ በጋድ ነገድ ይዞታ ውስጥ ባለችው በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትንና በምናሴ ነገድ ይዞታ ውስጥ በባሳን የምትገኘውን ጎላንን ለዩ።

9 ሳያስበው በድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ወደ ተለዩት ከተሞች መሸሽ ይችላል፤ በማኅበሩ ፊት ከመቆሙ አስቀድሞም በደም ተበቃዩ መገደል የለበትም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *