ዕዳ የሚተውበት ዓመት
1 በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ።
2 አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ እያንዳንዱ አበዳሪ ለእስራኤላዊ ባልንጀራው ያበደረውን ይተውለት፤እግዚአብሔር(ያህዌ)የዕዳ ምሕረት አውጆአልና፣ አበዳሪው፣ እስራኤላዊ ባልንጀራውን ወይም ወንድሙን ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው።
3 ለባዕድ ያበደርኸውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማናቸውንም ዕዳ ግን ተወው።
4 ይሁን እንጂ አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤
5 ይህ የሚሆነውም ለአምላክህለእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው።
6 አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።
7 አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች ባንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፣ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አታጨክንበት፤ ወይም እጅህን ወደ ኋላ አትሰብስብበት።
8 ይልቁንስ እጅህን ፍታለት፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ ቅር ሳይልህ አበድረው።
9 “ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቦአል” የሚል ክፉ ሐሳብ አድሮብህ፣ በችግረኛ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፣ እርሱም በአንተ ላይ ወደእግዚአብሔር(ያህዌ)ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!
10 በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠውም ልብህ አይጸጸት፤ ከዚህም የተነሣ አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በሥራህ ሁሉና እጅህ ባረፈበት በማናቸውም ነገር ይባርክሃል።
11 በምድሪቱ ላይ ድኾች ምንጊዜም አይጠፉም፤ ስለዚህ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞችህ፣ ለድኾችና ለችግረኞች እጅህን እንድትዘረጋ አዝሃለሁ።
አገልጋዮችን ዐርነት ማውጣት
12 ወገንህ የሆነ ዕብራዊ ወንድን ወይም ሴትን ገዝተህ ስድስት ዓመት ካገለገለህ፣ በሰባተኛው ዓመት ዐርነት አውጣው።
13 በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው።
14 ከመንጋህ፣ ከዐውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው፤ አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በባረከህ መጠን ስጠው።
15 አንተም ራስህ በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን ትእዛዝ ዛሬ የምሰጥህም በዚሁ ምክንያት ነው።
16 ነገር ግን አገልጋይህ፣ አንተንና ቤተ ሰብህን ከመውደዱና ከአንተም ጋር ደስተኛ ሆኖ ከመኖሩ የተነሣ፣ “ከአንተ መለየት አልፈልግም” ቢልህ፣
17 ጆሮውን ከቤትህ መዝጊያ ላይ በማስደገፍ በወስፌ ትበሳዋለህ፤ ከዚያም ዕድሜ ልኩን አገልጋይህ ይሆናል። በሴት አገልጋይህም ላይ እንደዚሁ አድርግ።
18 አገልጋይህን ዐርነት ማውጣቱ ከባድ መስሎ አይታይህ፤ የስድስት ዓመት አገልግሎቱ፣ አንድ የቅጥር ሠራተኛ የሚሰጠው አገልግሎት ዕጥፍ ነውና። አምላክህእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)በምታደርገው ነገር ሁሉ ይባርክሃል።
የእንስሳት በኵራት
19 የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎችህን ተባዕት በኵር ሁሉ ለአምላክህለእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ቀድስ። የበሬህን በኵር አትሥራበት፤ የበግህንም በኵር አትሸልት፤
20 እርሱ በሚመርጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህበእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)ፊት ትበሉታላችሁ።
21 አንድ እንስሳ እንከን ካለበት፣ አንካሳ ወይም ዕውር፣ ወይም ደግሞ ማናቸውም ዐይነት ከባድ ጒድለት ያለበት ከሆነ፣ ለአምላክህለእግዚአብሔር(ኤሎሂም ያህዌ)አትሠዋው፤
22 በየከተሞችህም ትበላዋለህ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነውም ሆነ ያልሆነው ሰው፣ እንደ ድኵላ እንደ ዋላ ይበላዋል።
23 ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።