ዘኁልቍ 12

ማሪያምና አሮን ሙሴን ተቃወሙ

1 ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት አግብቶ ነበርና ባገባት ኢትዮጵያዊት ምክንያት ማርያምና አሮን ይነቅፉት ጀመር።

2 እነርሱም፣ “ለመሆኑእግዚአብሔር(ያህዌ)የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አልተናገረም?” ተባባሉ፤እግዚአብሔርም(ያህዌ)ይህን ሰማ።

3 ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር።

4 ወዲያውእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን፣ አሮንንና ማርያምን፣ “ሦስታችሁም ውጡና ወደ መገናኛው ድንኳን ኑ” አላቸው፤ ሦስቱም ወጥተው ሄዱ።

5 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)በደመና ዐምድ ወረደ፤ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፣

6 እንዲህ አላቸው፤ “ቃሌን አድምጡ፤

“የእግዚአብሔር(ያህዌ)ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር፣

በራእይ እገለጥለታለሁ፤

በሕልምም እናገረዋለሁ።

7 ለአገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤

እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።

8 እኔ ከእርሱ ጋር የምነጋገረው ፊት ለፊት ነው፤

በግልጽ እንጂ በልዩ ዘይቤ አይደለም፤

እርሱየእግዚአብሔርን(ያህዌ)መልክ ያያል።

ታዲያ እናንተ አገልጋዬን ሙሴን

ትቃወሙ ዘንድ ለምን አልፈራችሁም?”

9 የእግዚአብሔር(ያህዌ)ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እርሱም ትቶአቸው ሄደ።

10 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ፣ እነሆ፤ ማርያም በለምጽተመታች፤ እንደ በረዶም ነጣች። አሮንም ወደ እርሷ ዘወር ሲል ለምጽ ወርሶአት አየ፤

11 ሙሴንም እንዲህ አለው፣ ‘ጌታዬ ሆይ፤ በስንፍናችን የሠራነውን ኀጢአት እባክህ አትቊጠርብን።

12 እርሷንም በእናቱ ማሕፀን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋላ የተወለደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ።”

13 ስለዚህም ሙሴ፣ “አምላክ(ኤሎሂም)ሆይ፤ እባክህ ፈውሳት” ብሎ ወደእግዚአብሔር(ያህዌ)ጮኸ።

14 እግዚአብሔርም(ያህዌ)ለሙሴ፣ “አባቷ እፊቷ ላይ ቢተፋባት እስከ ሰባት ቀን በኀፍረት መቈየት አይገባትምን? አሁንም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን እንድትገለል አድርግ፤ ከዚያ በኋላ ግን ልትመለስ ትችላለች” ሲል መለሰለት።

15 ስለዚህም ማርያም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተገለለች፤ ከዚያ እስክትመለስም ሕዝቡ ጒዞውን አልቀጠለም ነበር።

16 ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተነሣ፤ በፋራን ምድረ በዳም ሰፈረ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *