ዘሌዋውያን 12

ከወሊድ በኋላ የመንጻት ሥርዐት

1 እግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ሴት አርግዛ ወንድ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ትረክሳለች።

3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዝ።

4 ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቆይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ።

5 ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቆይ።

6 “ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻትዋ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ።

7 ካህኑምበእግዚአብሔር(ያህዌ)ፊት ያቅርበው፤ ያስተሰርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች።

“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው።

8 ጠቦት ለማምጣት ዐቅምዋ ካልፈቀደ፣ ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰር ይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *