የዕጣን መሠዊያ
1 ዕጣን የሚጤስበት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ።
2 ርዝመቱና ጐኑ ባለ አንድ አንድ ክንድየሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት።
3 ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።
4 መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ።
5 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።
6 መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው።
7 “አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ።
8 ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑበእግዚአብሔር(ያህዌ)ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው።
9 በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስበት።
10 አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መስዋዕት ደም ጋር መደረግ አለበት፤ ይህምለእግዚአብሔር(ያህዌ)እጅግ ቅዱስ ነው።”
የማስተስረያ ገንዘብ
11 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን አለው፤
12 “የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆለእግዚአብሔር(ያህዌ)መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም።
13 ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅልመስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅልለእግዚአብሔር(ያህዌ)የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
14 ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ለእግዚአብሔር(ያህዌ)መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው።
15 ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆንለእግዚአብሔር(ያህዌ)መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለ ጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጉድሎ አይስጥ።
16 የማስተሰረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግበእግዚአብሔር(ያህዌ)ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”
የመታጠቢያ ሰን
17 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን አለው፤
18 “ለመታጠቢያ ከናስ ማስቀመጫው ጋር የናስ ሰን አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት።
19 አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል።
20 ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፤ እንዲሁምለእግዚአብሔር(ያህዌ)የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ፣
21 እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፤ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።”
ቅብዐ ዘይት
22 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን አለው፣
23 “ምርጥ ቅመሞችን፣ አምስት መቶ ሰቅልፈሳሽ ከርቤ፣ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጠጅ ሣር፣
24 አምስት መቶ ሰቅል ብርጒድ ውሰድ፤ ሁሉም እንደ መቅደሱ ሰቅልና አንድ የኢን መስፈሪያየወይራ ዘይት ይሁን፤
25 እነዚህን በቀማሚ እንደ ተሠራ እንደሚሸት ቅመም የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት አድርግ፤ የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት ይሆናል፤
26 ከዚያም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት፣
27 ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን፣
28 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሰኑን ከነመቆሚያው እንድትቀባበት ይሁን።
29 እጅግ የተቀደሱ ይሆኑም ዘንድ ቀድሳቸው፤ የሚነካቸውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።
30 ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ቅባቸው፤ ቀድሳቸውም።
31 ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ይህ የእኔ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል፤
32 በማንም ሰው ሰውነት ላይ አታፍስሱት፤ በተመሳሳይ መንገድ ምንም ዘይት አትሥሩ፤ የተቀደሰ ነው፤ ቅዱስ መሆኑን ልብ በሉ።
33 ተመሳሳይ ዐይነት የሠራና ከካህናት ሌላ በማንም ሰው ላይ ያፈሰሰ ሁሉ ከወገኑ ይወገድ።
ዕጣን
34 ከዚያምእግዚአብሔር(ያህዌ)ሙሴን አለው፤ “ተመጣጣኝ በማድረግ የጣፋጭ ሽቱ ቅመሞች፣ የሚንጠባጠብ ሙጫ፣ በዛጐል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፣ የሚሸት ሙጫ፣ እና ንጹሕ ዕጣን ወስደህ፣
35 በቀማሚ እንደ ተሠራ ጣፋጭ መዐዛ ያለው የተቀመመ ዕጣን አብጅ፤ በጨው የተቀመመ፣ ንጹሕና የተቀደሰ ይሁን።
36 ከእርሱም ጥቂቱን ወቅጠህ ዱቄት በማድረግ አልመህ በመገናኛው ድንኳን ከምስክሩ ፊት ለፊት ከአንተ ጋር በምገናኝበት ስፍራ አስቀምጠው፤ ለአንተ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል።
37 ለራስህ በዚያ ዐይነት መንገድ ምንም ዐይነት ዕጣን አታብጅ።ለእግዚአብሔር(ያህዌ)የተቀደሰ መሆኑን ልብ በል።
38 በመልካም ሽታው ይደሰት ዘንድ እርሱን አስመስሎ የሚሠራ ሁሉ ከወገኑ የተወገደ ይሁን።